ቻይና የቡድን 7 አገራትን የአቋም መግለጫ አወገዘች

  • ቪኦኤ ዜና

የቡድን 7 መሪዎች

በቡድን 7 አገራት የተካሄደው ጉባኤ “ጸረ ቻይና ዎርክሾፕ” ነው ሲል በቻይና የሚደገፈውና ግሎባል ታይምስ የተሰኘው ጋዜጣ ዛሬ በርዕሰ አንቀጹ ጽፏል።

በሂሮሺማ ጃፓን የተሰባሰቡት የቡድን 7 አገራት ቅዳሜ ዕለት ያወጡትን የአቋም መግለጫ ተከትሎ፣ ቻይና በአገሪቱ የሚገኙትን የጃፓን አምባሳደር ጠርታ ስታነጋር፣ በእንግሊዝ የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ ደግሞ አገሪቱ የቻይናን ስም ከማጥፋት እንድትቆጠብ ጠይቋል።

የቡድን 7 አገራቱ ቅዳሜ ዕለት ባወጡት የአቋም መግለጫ፣ ቻይና በታይዋን ላይ የምታደርገውን ዛቻ፣ የኑክሌር ትጥቋን በተመለከተ እንዲሁም በዓለም ኢኮኖሚ ላይ አላት ያሉትን አሉታዊ ተጽእኖ አውግዘዋል።

“ቡድን 7 ወደ ጸረ ቻይና ዎርክሾፕነት ወርዷል” በሚል ርዕስ ግሎባል ታይምስ ባወጣው ርዕሰ አንቀጽ፣ አሜሪካ በምዕራቡ ዓለም ጸረ ቻይና መረብ ለመዘርጋት እየጣረች ነው ብሏል።

የቻይናው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የቡድን 7 አገራቱ ያወጡትን መግለጫ መቃወሙን አስመልክቶ፣ በአገሪቱ የሚገኙትን የጃፓን አምባሳደር ጠርቶ አነጋግሯል።

በዩክሬን ላይ በምታካሂደው ጦርነት ምክንያት በቡድን 7 ጉቤኤ ላይ የተወገዘችው ሩሲያም፣ ጉባኤው “የጸረ ሩሲያና የጸረ ቻይና አቋሞች መፈልፈያ ነው” ብላለች፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከቻይና ጋር ያለው የሻከረ ግኑኝነት በቅርቡ ይሻሻላል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

ቤጂንግ የቡድን ሰባቱን መግለጫ በተመለከተ ፈጣን ምላሽ በሰጠችበት ሁኔታ፣ ውጥረቱ ወዲያውኑ ይረግባል ብለው እንደማይጠብቁ ተንታኞች በመናገር ላይ ናቸው።