ባይደን ፖላንድ ጉብኝት ላይ ናቸው

  • ቪኦኤ ዜና
ፕሬዚዳንት ባይደን በፖላንድ ዋና ከተማ ዎርሶው

ፕሬዚዳንት ባይደን በፖላንድ ዋና ከተማ ዎርሶው

በዩክሬን ዋና ከተማ ኪየቭ ትናንት በድንገት ጉብኝት ያደረጉት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ወደ ፖላንድ ተጉዘዋል።

ፕሬዚዳንት ባይደን ዛሬ በፖላንድ ዋና ከተማ ዎርሶው ከሚገኘው ታሪካዊ ቤተ መንግሥት ሩሲያ ዩክሬንን ላይ ወረራ የከፈተችበት አንደኛ ዓመት መታሰቢያን አስመልክተው የሚያደርጉት ንግግር በከፍተኛ ደረጃ እየተጠበቀ ነው።

ፕሬዚዳንት ባይደን በንግግራቸው የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ ሀገራቸውን ከጥቃት እንዲከላከሉ ለመርዳት ዩናይትድ ስቴትስ የኔቶ አባል ሀገሮች እና ምዕራቡን ዓለም ምን ያህል እንዳስተባበረች አጉልተው ያስረዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኋይት ሐውስ የብሄራዊ ጸጥታ አማካሪ ጄክ ሰለቫን በሰጡት ቃል ፕሬዚዳንት ባይደን በዚሁ ቦታ ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ንግግር ማድረጋቸውን አስታውሰው የዛሬውም ንግግራቸው ኔቶ እና ዩናይትድ ስቴትስ ለዩክሬን እየሰጡ ስላለው ድጋፍ መሰረታዊ ጥያቄዎችን የሚመልስ እንደሚሆን አስረድተዋል።

ባይደን ከአንድ ዓመት በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ በፖላንድ ያደረጉትን ጉብኝት ከፕሬዚዳንት አንደርዜጅ ዱዳ ጋር በመወያየት ጀምረዋል።