ፖሊስ ሰሜናዊ ፈረንሳይ ውስጥ አንድ የአይሁዳውያን ምኩራብ በእሳት ለማጋየት ሲሞክር ያገኘውን ሰው ገደለ

የፖሊስ መኪና ከምኩራብ ፊት ለፊት ቆሟል፤ ሩዋን ከተማ፣ ፈረንሣይ እአአ ግንቦት 17/2024

የፈረንሳይ ፖሊስ ዛሬ አርብ በሰሜናዊቱ የሩዋን ከተማ የሚገኝ የአይሁዳውያን ምኩራብ ለማቃጠል የሞከረ ግለሰብ ተኩሶ መግደሉን አስታወቋል። ግለሰቡ ወደ አካባቢው የመጣውን ፖሊስ በተጋፈጠበት ወቅት ስለት እና የብረት ዘንግ ይዞ እንደነበር እና የፖሊስ ኃይል የወሰደውን እርምጃ ተከትሎም ወዲያውኑ ህይወቱ ማለፉን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ገልጠዋል።

የፈረንሳይ የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትር ጀራልድ ዳርማኒን በበኩላቸው በX ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ “ሮዋን ያለው የብሔራዊ ፖሊስ ኃይል ዛሬ ማለዳ ከተማይቱ ውስጥ የሚገኘውን ምኩራብ ሆን ብሎ በእሳት ለማጋየት የሞከረ አንድ ግለሰብ አስወግዷል” ብለዋል።

የከተማይቱ ከንቲባ ኒኮላስ ማየር-ሮሲኖል’ም በተመሳሳይ በኤክስ ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ "ጥቃቱ የተቃጣው በአይሁዳውያን ማሕበረሰብ ላይ ብቻ አይደለም። የስሜት ጉዳት የደረሰው በሩዋን ከተማ ሕዝብ በሙሉ ላይ ነው” ብለዋል። ከግለሰቡ በስተቀር በሌላ ሰው የደረሰ ጉዳት ያለመኖሩንም ከንቲባው ጨምረው አመልክተዋል።

በምኩራቡ ላይ የደረሰውን ጉዳት እና በግለሰቡ የተገደለበትን ሁኔታ በተመለከተ ሁለት የተለያዩ ምርመራዎች መከፈታቸውን ደግሞ ይፋ ያደረገው የሩዋን አቃቤ ህግ ነው። የፈረንሳይ ፖሊስ በወሰደው እርምጃ አንድ ግለሰብ በሚገደልበት ወቅት የፖሊስ ዋና ተቆጣጣሪ ይህን መሰል የወንጀል ምርመራ ወዲያውኑ መክፈት የተለመደ አሰራር ነው።

ፈረንሣይ እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ከ2015 አንስቶ በአይሁዳውያን ላይ የተነጣጠሩ ተደጋጋሚ የእስላማዊ ኃይሎች

ጥቃቶች ኢላማ ሆና መቆየቷ ይታወቃል። ባለፉት ቅርብ ወራት ውስጥም አንዳንድ የተናጠል ጥቃቶች መድረሳቸውን ተከትሎ የፈረንሳይ የደህንነት ጥበቃ ሥርአት በከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተመልክቷል።