አንድ የ17 ዓመት ሹፌር ፓሪስ ውስጥ በፖሊስ መገደሉን ተከትሎ በከተማዋና በሌሎችም ትላልቅ ከተሞች የተነሳው ተቃውሞ እንዲበርድ፣ እንዲሁም መረጋጋት እንዲኖር የጠየቀው የፈረንሣይ መንግስት፣ ብዛት ያለው የፖሊስ ኃይል ማሰማራቱንም ገልጿል፡፡
የሟቹ ናዬል ኤም ጠበቆች ግድያው ትናንት ማክሰኞ በትራፊክ ፍተሻ ወቅት የተፈጸመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በግድያ ወንጀል የተጠረጠረው የፖሊስ መኮንን በቁጥጥር ስር መዋሉንም አቃቤ ህግ ገልጿል።
ክስተቱን የሚያሳዩ ናቸው የተባሉት ተንቀሳቃሽ ምስሎች፣ አንደኛው ፖሊስ በመቆም ላይ በነበረው መኪና መስኮት በኩል ሲተኩስ አሳይተዋል።
ድርጊቱን ተከትሎ ሌሊቱን በተነሳው ተቃውሞ፣ 31 ሰዎች ሲታሰሩ፣ 25 ፖሊሶች መቁሰላቸውንና 40 ተሽከርካሪዎች መቃጠላቸውን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ግድያው እውቁን የፈረንሣይ የእግር ኳስ ኮከብ ኪሊያን ምባፔን ጨምሮ፣ አገር አቀፍ ውግዘትና ቁጣን መቀስቀሱን የአሶሽየትድ ፕሬስ ዘገባ አመልክቷል፡፡
አደጋው በደረሰበት ትናንት ሌሊት 1ሺ200 ፖሊሶች መሰማራታቸው ሲነገር መንግሥት ዛሬ ረቡዕ 2ሺ ፖሊሶች በፓሪስ እና በሌሎች ትላልቅ ከተሞች “ሥርዓት ለማስከበር” እንደሚሰማሩ አስታውቋል፡፡