ኒዤርን ለቆ የወጣው የመጀመሪያው ዙር የፈረንሣይ ወታደሮች አጀብ፣ ከዘጠኝ ቀናት ጉዞ በኋላ ቻድ መድረሱ ተነግሯል።
አጀቡ ካለምንም ችግር ቻድ መድረሱን የፈረንሣይ ጦር አስታውቋል። ወታደሮቹ ከቻድ ወደ ፈርንሣይ በአየር እንደሚጓዙ ታውቋል።
በሳህል ቀጠና፣ የፈረንሣይ አጋር በነበረችው ኒዤር፣ ፕሬዝደንት ሞሃመድ ባዙም ባለፈው ሐምሌ በመፈንቅለ መንግስት ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ፣ ሁንታው የፈረንሣይ ጦር ሀገሪቱን ለቆ እንዲወጣ ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር። እርምጃው ፈረንሣይ በአካባቢው ያላት ተጽእኖ እንዲያከትም አድርጓል ተብሏል።
የፈረንሣይ ጦር ወታደራዊ መሣሪያዎቹን፣ በምድር በቻድ በማድረግ ወደ ካሜሩን ማሻገር እንደሚጠበቅበት፣ ይህም 3ሺሕ ኪ.ሜ. ርቀት ሲኖረው፣ አካባቢው የጂሃዲስት ቡድኖች የሚንቀሳቀሱበት እንደሆነ ታውቋል።
ከአል ቃይዳ ጋር ግንኙነት ያላቸውን እስላማዊ አክራሪ ቡድኖች ለመፋለም በሚል፣ ፈረንሣይ 1ሺሕ 400 የሚሆኑ ወታደሮቿን መኒያሜይ እና በምዕራብ ኒዤር አስፍራ ነበር።