የአሜሪካ የነፃነት ቀን ወይም በተለምዶ በሚውልበት ቀን እንደሚጠራው “ፎርዝ ኦፍ ጁላይ” ነገ ተክብሮ ይውላል።
ቀኑ የአሜሪካ ኮንግረስ በእ.አ.አ ጁላይ 4፣ 1776 ዓ/ም በእንግሊዝ ሥር የነበሩት ቅኝ ግዛቶች ነፃ መውጣታቸው የታወጀበትን ሰነድ በሙሉ ድምፅ ያጸደቀበት ነው።
ከአንድ ዓመት በኋላ በፊላደልፊያ ቀኑ ተከብሮ የነበረ ቢሆንም፣ ለቀጣዩ አርባ ዓመታት እምብዛም ሳይከበር ቀርቶ፤ በ1812 በአሜሪካና አጋሮቿ በአንድ ወገን እንዲሁም በእንግሊዝና በአጋሮቿ በሌላ ወገን የተካሄደውን ጦርነት ተከትሎ እንደገና በስፋት መከበር ጀምሯል። የአሜሪካ ኮንግረስ ዘግይቶም ቢሆን በእ.አ.አ 1870 ቀኑ የፌዴራል በዓል እንዲሆን ወስኗል።
በዕለቱ የመንግስት ሕንጻዎች፣ ፖስታ ቤቶች፣ ፍርድ ቤቶችና ት/ቤቶች ዝግ ይሆናሉ። ባንኮችና የአክሲዮን ገበያዎችም ይዘጋሉ።
በቀኑ እና ተያይዞ ባለው የሣምንት መጨረሻ አሜሪካውያን በብዛት ረዥምም ሆነ አጭር ጉዞ የሚያደርጉ ሲሆን፣ በያዝነው ሳምንት 60.6 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በመኪና ወደ ዕረፍት ማድረጊያና መዝናኛ ስፍራዎች ሲያመሩ፣ ከ5.7 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሠዎች ደግሞ በአየር ይበራሉ። ከምስጋና ቀን “ታንክስ ጊቪንግ” በዓል ለጥቆ አሜሪካውያን በብዛት የሚጓዙብት አጋጣሚ ነው።