ምስራቅ አፍጋንስታን ውስጥ 40 ሰዎች በከባድ ዝናም፣ 17 ሰዎች በተሽከርካሪ አደጋ ሕይወታቸው አጡ

ምስራቅ አፍጋንስታን ውስጥ በጣለው ከባድ ዝናም 40 ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ፤ ቁጥራቸው 350 የሚጠጋ ሌሎች የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል።

የታሊባን ባለ ሥልጣናት እንዳስታወቁት፤ ምስራቅ አፍጋንስታን ውስጥ በጣለው ከባድ ዝናም 40 ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ፤ ቁጥራቸው 350 የሚጠጋ ሌሎች የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል። የናንጋርሃር ክፍለ ግዛት ቃል አቀባይ ጨምረው እንዳስረዱት፤ ከሞቱት ውስጥ የመኖሪያ ቤታቸው ጣሪያ በላያቸው ላይ የተደረመሱ አምስት የአንድ ቤተሰብ አባላት ይገኙበታል። ሌሎች አራት የቤተሰቡ አባላትም የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸው ተመልክቷል።

በተጨማሪም 400 የሚደርሱ የመኖሪያ ቤቶች እና 60 የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች የወደሙ ሲሆን፤ በጠቅላይ ግዛቲቱ ዋና ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት መቋረጡ ተዘግቧል። በሌላ ዜና፣ አንድ አውቶቡስ ተገልብጦ 17 ሰዎች ሲገደሉ፤ 34 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን የሃገሪቱ የዜና ማሰራጫ ዘግቧል።