የቀድሞው የሰላም ሚኒስትር ደ’ኤታ አቶ ታዬ ደንደኣ፣ ዛሬ ኀሙስ፣ ሚያዝያ 17 ቀን 2016 ዓ.ም.፣ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሕገ መንግሥት እና የሕገ መንግሥት ሥርዓት ችሎት ቀርበው የወንጀል ክስ እንደተመሠረተባቸው፣ ጠበቃቸው ዶክተር ቶኩማ ዳባ ለአሜሪካ ድምፅ ገልጸዋል፡፡
ዐቃቤ ሕግ በደንበኛቸው ላይ ሦስት ክሶችን ማቅረቡን የገለጹት ጠበቃቸው፣ “የፀረ ሰላም ኀይሎችን የሚደግፉ የፕሮፓጋንዳ መልእክቶችን በስማቸው በተከፈተ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ላይ በማስተላለፍና ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ይዞ በመገኘት” የሚሉ የወንጀል ክሶች እንደተመሠረተባቸው አስረድተዋል፡፡
ባለፈው ታኅሣሥ ወር፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከኃላፊነታቸው ከተነሡ በኋላ በፌደራል የጸጥታ እና የፀረ ሽብር ግብረ ኀይል በቁጥጥር ሥር የዋሉት አቶ ታዬ፣ ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ ያለጠበቃ ብቻቸውን በችሎቱ ቀርበው እንደነበረ ዶር. ቶኩማ አውስተው፣ ፍርድ ቤቱ ለዛሬ ከጠበቃቸው ጋራ ይቅረቡ፤ የሚል ብይን በመስጠቱ መቅረባቸውን አስረድተዋል፡፡
ምርመራው ባለፈው ታኅሣሥ 24 ቀን መጠናቀቁንና ክሱ ዘግይቶ መቅረቡን አስመልክቶ ተቃውሞ ማቅረባቸውን የገለጹት ጠበቃቸው፣ ስለ ጉዳዩ በችሎቱ የጠየቀው ዐቃቤ ሕግ በቂ የሚባል ምላሽ አልሰጠም፤ ብለዋል፡፡ የደንበኛቸው የዋስ መብት እንዲጠበቅላቸው መጠየቃቸውንም የተናገሩት ጠበቃቸው፣ ፍርድ ቤቱ መርምሮ ብይን ለመስጠትና ምናልባት በክሱ ላይ ተቃውሞ ካለን ለመስማት፣ ለሚያዝያ 24 ቀን 2016 ዓም. ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን ጠቁመዋል፡፡
በዛሬው ችሎት አቶ ታዬ፡- ከጠበቃቸው፣ ከቤተሰባቸው እና ከሃይማኖት አባታቸው ጋራ መገናኘት አለመቻላቸውን እንዲሁም ለብቻቸው በጨለማ ቤት መታሰራቸውን በመጥቀስ በቃል አቤቱታ አቅርበዋል፡፡
ችሎቱም፣ አቶ ታዬ ጠበቆቻቸውን፣ የሃይማኖት አባቶችንና ቤተሰቦቻቸውንና ሌሎች ዘመዶቻቸውንም ለማግኘት እንዲችሉ፤ እንደ ማንኛውም ታራሚም ለብቻቸው ሳይኾን ከሌሎች ታራሚዎች ጋራ እንዲያቆያቸው ለፌደራል ፖሊስ ትእዛዝ ማስተላለፉን ጠበቃቸው አስረድተዋል።
በተጨማሪም፣ ቤተሰቦቻቸው ከመንግሥት የኪራይ ቤት መባረራቸውንና የቤተሰባቸው የባንክ የቁጠባ ሒሳብ መታገዱን አስመልክቶ አቶ ታዬ በቃል ለችሎቱ ያቀረቡትን አቤቱታ፣ ፍርድ ቤቱ በጽሑፍ እንዲያቀርቡ ማዘዙን ገልጸዋል፡፡