እስራኤል ከጋዛ “ወረራ” ከተገታች ሐማስ ሁሉንም ታጋቾች እንደሚለቅ የቀድሞ መሪው ተናገሩ

  • ቪኦኤ ዜና

የቀድሞው የሐማስ መሪ ካሊድ ማሻል

የቀድሞው የሐማስ መሪ ካሊድ ማሻል፣ ትላንት ሰኞ፣ ለስካይ ኒውስ ጣቢያ ሲናገሩ፥ እስራኤል በጋዛ ሰርጥ የምታደርገውን “ጥቃት” ካቆመች፣ የሐማስ ታጣቂዎች፣ ባለፈው መስከረም 26 እስራኤልን በድንገት ባጠቁበት ቀን አግተው የወሰዷቸውን ሰዎች እንደሚለቁ ተናገሩ።

ማሻል አክለውም፣ “ጥቃቱን ያቁሙና በኳታር፣ በግብጽ እና በሌሎች የአረብ ሀገራት ሽምግልና፣ ታጋቾቹ የሚለቀቁበትን መንገድ ፈልገው፣ ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ እናደርጋለን፤” ብለዋል።

ሐማስ እና ሌሎች የጋዛ ታጣቂዎች፣ ቁጥራቸው በውል ያልተረጋገጠ የሌሎች ሀገራት ዜጎችንና ጥምር ዜግነት ያላቸውን ግለሰቦች ጨምሮ 220 የሚደርሱ ሰዎችን አግተው እንደወሰዱ ይታመናል።

ማሻል፣ በኳታር ዶሃ ውስጥ በሰጡት በዚኽ አስተያየት፣ ጦርነቱ ተቀስቅሶ፣ እስራኤል በፍልስጥኤም ላይ በፈጸመችው የቦምብ ጥቃት፣ ከ22 በላይ ሰዎች ከተገደሉ በኋላ፣ ታጋቾቹ ወደተለያዩ ቦታዎች እንደተወሰዱ አመልክተዋል።

ሐማስ፣ ትላንት ሰኞ ምሽት፣ በዕድሜያቸው የገፉ ሁለት እስራኤላውያት አረጋውያን ታጋቾችን እንደለቀቀ ይታወቃል።

በጋዛ ድንበር አቅራቢያ የምትገኘው ኒር ኦዝ የተባለች የገበሬ መንደር ነዋሪዎች የኾኑት ሁለቱ ሴቶች፣ ሐማስ ደቡባዊ እስራኤልን በወረረበት ወቅት፣ ከባለቤቶቻቸው ጋራ ታግተው ከተወሰዱት ውስጥ ናቸው፡፡ ባሎቻቸው ግን፣ እስከ አሁንም እንደታገቱ ናቸው።