የጀርመን ቻንስለር አንገላ መርከል በፍልሰተኞች ጉዳይ ዙሪያ ከአጎራባች ሀገሮች ጋር እንደሚነጋገሩ ማስታወቃቸውን ተከትሎ የወቅቱን የአውሮፓ የኢሚግሬሽን ቀውስ ለጊዜውም ቢሆን ለመቀለበስ ተችሉዋል። መርክል ይህን ያደረጉት የገዢው ጥምረታቸው ያሉት ወግ አጥባቂዎቹ የሀገሪቱን የጥገኝነት ደንቦች እንዲያጠብቁ የሁለት ሳምንት ጊዜ መስጠታቸውን ተከትሎ ነው።
ጀርመን ብቻዋን ፍልሰተኞችን ከድንበርዋ እንድትመልስ አልፈልግም ሲሉ መርክል ቢናገሩም የሀገር ግዛት ሚኒስትሩ ሀርስት ሲሆፈር ፍልሰተኞች መቀበል እንዲከለከል እደግፋለሁ ሲሉ መሰማታቸው በሁለቱ ወግ አጥባቂ ፓርቲዎች መካከል ለሰባ ዓመታት ፀንቶ የኖረውን ህብረት ሊያፈርስ ይችላል የሚል ሥጋት ደቅኑዋል።
ጀርመን ከራሱዋ ድንበር ፍልሰተኛውን ብትመልስ በተቀረው የአውሮፓ አካባቢ አሉታዊ ውጤት ያስከትላል ሲሉ ነው መርክል ያስረዱት።
የሀገር ግዛት ሚኒስትሩ ፓርቲ የሆነው የባቫሪያ ክሪስቲያን ሶሾል ህብረት ፓርቲ በሊሎች የአውሮፓ ህብረት ሀገሮች የተመዘገቡ ፍልሰተኞች ጀርመን እንዳይገቡ የሚከለክለውን ዕገዳ እስከመጪው ሃምሌ ወር ለማዘግየት ያቀረበውን ሃሳብ መርክል ተቀብለውታል።
ከሜክሲኮ ጋር በሚያዋስነው የዩናይትድ ስቴትስ ድንበር በህገ ወጥ መንገድ ለመግባት ከሚሞክሩ ፍልሰተኞች ላይ ከልጆቻቸው በሚለያየው የአስተዳደራቸው ፖሊስ ተቃውሞ እየበረታባቸው ያሉት ፕሬዚደንት ዶናልድ ትረምፕ ፍልሰተኞች ያለገደብ ወደአውሮፓ እንዳይገቡ የሚደረገውን ትግል ደግፈው ተናግረዋል።