‹‹ስቃዩን ተቋቁመው እኛ ጋር የሚደርሱት የተወሰኑት ብቻ ናቸው›› ዶ/ር አምባዬ ወልደ ሚካኤል

dr. ambaye wolde michael

ዶ/ር አምባዬ ወልደ ሚካኤል የማሕጸንና ጽንስ ባለሞያ ናቸው፡፡ሥራ በጀመሩበት አዲስ አበባ ፌስቱላ ሆስፒታል ዐስራ አራት ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በዚህ ቆይታቸው በሞያቸው ከሚያገለግሏቸው ሴቶች በተጫማሪ በሆስፒታሉ ውስጥ አንድ ቡድን በማዋቀር ከአዲስ አበባ ውጪ በሦስት ቦታዎች የፌስቱላ ሕክምና አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ማዕከላትን አቋቁመዋል፡፡

ዶ/ር አምባዬ አሁን በሴቶችና ጤና ላይ የሚሠራ ዓለም አቀፍ ተቋም (Women and Health Alliance International) ውስጥ ባለሞያ ናቸው፡፡ ከዚህ ቷቋም እና ከዩኒቨርስቲዎች ጋር በመተባባርም በሦስት የኒቨርስቲዎች ውስጥ ፌስቱላን ለመከላከል እንዲሁም ተጎጂዎችን ለማከም የሚያስችል የባለሞያዎች ማሰልጠኛ ማዕከል እንዲገነባ አስችለዋል፡፡

ዶ/ር አምባዬ በኢትዮጵያ፣ታንዛኒያ፣ኡጋንዳ፣ዙምባብዌን ጨምሮ በአፍጋኒስታና በሌሎች አገራት ተጉዘው የህክምና አገልግሎት እና የማስተማር ሥራ ይሠራሉ፡፡ በሞያቸው በቆዩበት ዓመታት ውስጥ የቅርብ ጊዜ የቁጥር መረጃ ባይኖራቸውም እስከሚስታዉሱት ድረስ ለሰባት ሺሕ የፌስቱላ ታማሚዎች የቀዶ ጥገና ሕክምና ሰጥተዋል፡፡

‹‹ዕድል ቀንቷቸው የደም መፍሰሱን፣የማሕጸን ቁስለቱን እና ሕመሙን ተቋቁመው እንዲሁም ሆስቲታል የሚደርሱበት መጓጓዣ አግኝተው እኛ ጋር በመምጣት ሕክምናውን የሚያገኙት ሴቶች ዕድለኞች ናቸው፡፡ የቀሩት እንዲሁ በየሜዳው ይቀራሉ›› ይላሉ ዶ/ር አምባዬ ስለ ኢትዮጵያ የፌስቱላ ሕመምተኞች ሲናገሩ፡፡

ዶ/ር አምባዬ በዚህ ሞያቸው ላበረከቱት አስተዋፆ ከወራት በፊት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ሲያበረክትላቸው ሰሞኑን ደግሞ ካናዳ የሚገኘው ዓለም አቀፍ የማኅጸንና ጽንስ ማኅበር ሽልማት ሰጥቷቸዋል፡፡

ጽዮን ግርማ ዶ/ር አምባዬ ወልደ ሚካኤልን አነጋግራ የሠራችውን ዘገባ ከተያያዘው ድምጽ ማድመጥ ትችላላችሁ፡፡

Your browser doesn’t support HTML5

‹‹ስቃዩን ተቋቁመው እኛ ጋር የሚደርሱት የተወሰኑት ብቻ ናቸው›› ዶ/ር አምባዬ ወልደ ሚካኤል/ርዝመት-10ደ30ሰ/