ፊንላንድ፣ በዛሬው ዕለት፣ 31ኛው የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት(ኔቶ) አባል ኾና ስትመዘገብ፣ ከሩሲያዋ ክሬምሊን ቁጣ የተሰማ ሲኾን፣ የአጸፋ ርምጃ እንደሚኖርም አስታውቃለች።
ባለፈው ዓመት፣ ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ፣ በአውሮፓ ያለው የጸጥታ ኹኔታ ሲቀየር፣ ወታደራዊ ጉዳይን በተመለከተ፣ ለዐሥርት ዓመታት ያለውግንና በተዐቅቦ የቆዩት ፊንላንድ እና ስዊድን፣ ሐሳባቸውን እንዲቀይሩ አድርጓል።
“ከጥቂት ዓመታት በፊት፣ ፊንላንድ የኔቶ አባል ትኾናለች ብለን አናስብም ነበር። አሁን የጦር ቃል ኪዳኑ ሙሉ አባል ናት። ይህ ታሪካዊ ነው፤” ብለዋል የኔቶው ዋና ጸሐፊ ጀንስ ስቶልተንበርግ።
ከጥቂት ዓመታት በፊት፣ ፊንላንድ የኔቶ አባል ትኾናለች ብለን አናስብም ነበር። አሁን የጦር ቃል ኪዳኑ ሙሉ አባል ናት። ይህ ታሪካዊ ነው፤”
“ኔቶ፥ ፊንላንድን ለመከላከል ዝግጁ ይኾን እንደሁ፣ ጥርጣሬ ላላት ሞስኮ ግልጽ ኾኗል። ፊንላንድ አሁን ደኅንነቷ የተጠበቀ ነው፤” ሲሉ አክለዋል ስቶልተንበርግ።
የፊንላንዱ የመከላከያ ሚኒስትር አንቲ ካይኮነን በበኩላቸው፣ “ኹሉም ወገኖች አሸናፊ የኾኑበት ውሳኔ ነው፤” ብለዋል።
ሞስኮ በበኩሏ፣ ውሳኔው፣ በአገሪቱ ጸጥታ እና ብሔራዊ ጥቅም ላይ የተቃጣ ርምጃ ነው፤ ብላለች።
“ይህ ከስትራቴጂም ኾነ ከታክቲክ አንጻር፣ የአጠፌታ ርምጃ እንድንወስድ ያስገድደናል፤” ብለዋል የክሬምሊን ቃል አቀባይ ድሚትሪ ፔስኮቭ።
ፊንላንድ ኔቶን በመቀላቀሏ፣ “በአንድ አባል ላይ የተቃጣ ጥቃት፣ በኹሉም አባላት ላይ እንደተቃጣ ጥቃት ተደርጎ ይቆጠራል፤” በሚለው የጦር ቃል ኪዳን ድርጅቱ ስምምነት፣ አንቀጽ አምስት መሠረት መከታዋን አግኝታለች።