በሱዳን ውጊያው ቀጥሏል፣ የሟቾች ቁጥር ከ100 አሻቀበ

ካርቱም ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች ፍንዳታዎች ታይተዋል፡፡

በኹለቱ ተፎካካሪ የሱዳን ጀነራሎች መሀከል፣ ባለፈው ቅዳሜ የተጀመረው ውጊያ፣ ለዛሬ ሦስተኛ ቀን ሰኞ ቀጥሎ፣ የሱዳን መዲና ካርቱም በፍንዳታዎች ስትናጥ ውላለች። የሟቾች ቁጥር፣ ከ100 እንዳለፈ በመነገር ላይ ነው፡፡

የሱዳን ጦር ጠቅላይ አዛዥ ጀነራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሃንና የፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይል ወይም በምሕጻረ ቃሉ - አርኤስኤፍ በሚል የሚጠራው ኃይል አዛዥ የኾኑት ጀነራል ሞሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ፣ ከኹለት ዓመታት በፊት በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ቢይዙም፣ በሽግግር መንግሥት ሒደት፣ በተለይም አርኤስኤፍ ወደ መደበኛ ሠራዊት ስለሚዛወርበት ጊዜ አስመልክቶ መግባባት ላይ ባለመድረሳቸው ወደ ትጥቃዊ ግጭት አምርተዋል፡፡

ሕዝብ በብዛት በሚኖርባቸው በመዲናዋ ካርቱም እና በሌሎች ከተሞች በሚካሔደው ውጊያ፥ የአየር፣ የታንክ እና የከባድ መሣሪያ ጥቃቶች ተስተውለዋል፡፡ እስከ አሁን 97 ሰዎች እንደ ሞቱ፣ የአገሪቱ የዶክተሮች ኅብረት አስታውቋል፡፡ የሱዳን ሐኪሞች ማዕከላዊ ኮሚቴ የተባለው ሌላው ተቋም ደግሞ፣ በደርዘን የሚቆጠሩ የጸጥታ ኃይሎች መሞታቸውንና 942 ደግሞ መቁሰላቸውን ገልጿል፡፡

ግጭቱ በአስቸኳይ እንዲቆም ዓለም እየተማፀነ ይገኛል፡፡

ኹለቱ ወገኖች፣ ትላንት እሑድ፣ የተጎዱ ሰዎችን ለማንሣት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካይነት ቢስማሙም፣ የከባድ መሣሪያ ተኩስ አልቆመም ነበር፡፡

በካርቱም የሚገኙትና በሱዳን የተመድ ልዩ መልእክተኛ ቮልከር ፐርዝስ፣ ኹለቱ ወገኖች ለሰብአዊ ተግባር ሲባል ተኩስ ባለማቆማቸው፣ “እጅግ መበሳጨታቸውን” ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡

ካርቱም ውስጥ ከሚገኙት ዘጠኝ ሆስፒታሎች ውስጥ፣ አብዛኞቹ የደም እና አስፈላጊ መሣሪያዎች እጥረት እንደገጠማቸው፣ የዓለም ጤና ድርጅት ከወዲሁ አስጠንቅቋል፡፡

ጃንጃዊድ ሚሊሺያ ከተባለው ቡድን የወጣው አርኤስኤፍ፣ ከዐሥር ዓመታት በፊት፥ በወቅቱ የአገሪቱ መሪ በነበሩት ኦማር ሐሰን አልበሺር የተቋቋመ ሲኾን፣ በምዕራብ ዳርፉር ክልል፣ “አረብ ያልኾኑ ኅዳጣን ማኅበረሰቦችን ለማጥቃት በመጠቀም የጦር ወንጀል ፈጽመዋል፤” የሚል ክሥ ቀርቦባቸው ነበር።