የፌስቡክ እናት ድርጅት ሜታ ለሁለተኛ ጊዜ 10ሺ ሠራተኞችን አባረረ

የፌስቡክ እናት ኩባንያ ሜታ ዋና መሥሪያ ቤት፤ ካሊፎርኒያ

የፌስቡክ እናት ኩባንያ ሜታ ፕላትፎርምስ 10ሺ ሠራተኞችን ከሥራ ማሰናበቱን ዛሬ ማክሰኞ አስታወቀ፡፡

ሜታ ይህን ያስታወቀው 11ሺ ሠራተኞችን ማባረሩን ካስታወቀ አራት ወራት በኋላ ነው፡

ይህን በማድረጉም ለሁለተኛ ጊዜ ሠራተኞችን በገፍ ማበረሩን የገለጸ የመጀመሪያው ትልቁ የቴኮኖሎጂ ድርጅት መሆኑን ሮይተርስ በዘገባው አመልክቷል፡፡

“ሠራተኞቻችንን በ10ሺዎች በመቀነስ፣ አዳዲስ ለሚኖሩን የሥራ መስኮችና እስካሁን ያልቀጠርናቸውን 5ሺ ተጨማሪ ክፍት የሥራ መደቦችን እንሞላለን ብለን እንጠብቃለን” ሲሉ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማርክ ዙከርበርግ ለሠራተኞቻቸው በላኩት መልዕክት አስታውቀዋል፡፡

የሠራተኞቹ ቅነሳ፣ አነስተኛ ትኩረትና ቅድሚያ የሚሰጣቸው ፕሮጀክቶችን በመሰረዝ፣ የቅጥር መጠንን በመቀነስ ሜታን እንደገና ለማዋቀር የሚደረገው ትልቅ እቅድ አካል መሆኑ ተመልክቷል፡፡

ዜናው የሜታን አክሲዮን ዋጋ በ 2ከመቶ ከፍ ማድረጉ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡

እርምጃው ዙከርበርግ እኤአ 2023 “የውጤት ዓመት” እንዲሆን በማሰብ ከ89 እስከ 95 ቢሊዮን ዶላር ከሚደርሰው ወጭ የ5 ቢሊዮን ዶላር ቅነሳ ለማድረግ የጀመሩትን ግፊት የሚያጎላው መሆኑን ተመልክቷል፡፡

እየተበለሻ የመጣው ኢኮኖሚ፣ በአሜሪካ በሚገኙ ትላልቅ ኩባንያዎች፣ እንደ ጎልድማን ሳክስ እና ሞርገን ስታንሊ የመሳሰሉትን የዎል ስትሪ ባንኮች ጨምሮ እንደ አማዞን እና ማይክሮ ሶፍት በመሳሰሉ ትላልቆቹ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች ዘንድ ከባድና ተከታታይ የጅምላ ስራ ቅነሳዎችን እያስከተለ ነው፡፡

የቴክኖሎጂ ድጅርቶች እኤአ ከ2022 ጀምሮ 280ሺ ሠራተኞችን ያባረሩ ሲሆን ፣ከዚህ ውስጥ 40 ከመቶ የሚሆኑት የተባበረሩት በዚህ በያዝነው የ2023 ዓመት መሆኑን ከሥራ ገበታቸው የተቀነሱ ሠራተኞችን የሚከታተለው ተቋም አስታውቋል፡፡

መጭውን ሜታ ቨርስ ለመገንባት ብዙ ቢሊዮን ዶላሮችን ያፈሰሰው ሜታ፣ ከኮቪድ ወረርሽኝ በኋላ በዋጋ ግሽበትና የወለድ መጠን ከተመቱ ድርጅቶቹ ያገኛቸው የነበሩት የማስታወቂያ ገቢዎች ማሽቆልቆላቸው ተነግሯል፡፡