አሜሪካ ሱዳንን ያተራምሳሉ ባለቻቸው ግለሰቦች ላይ ማዕቀብ ጣለች

  • ቪኦኤ ዜና
የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እ.አ.አ በ1997፣ በሱዳን ላይ ተጥሎ የነበረውን ማዕቀብ በማስፋት፣ በሱዳን፥ የዴሞክራሲ ሽግግርን አደናቅፈዋል፤ አገሪቱን ለትርምስ ዳርገዋል ባሏቸው ግለሰቦች ላይ በዛሬው ዕለት ማዕቀብ ጥለዋል፡፡

የሱዳን መንግሥትን ንብረት የሚያግደውና ከአገሪቱ ጋራ የሚደረግን የንግድ ልውውጥ የሚከለክለው እ.አ.አ. በ1997 የተጣለውን ማዕቀብ፣ ፕሬዚዳንቱ፣ በዐዲስ መልክ ማጠናከራቸውን፣ ዛሬ ከዋይት ኃውስ የወጣው መግለጫ አመልክቷል፡፡

በሱዳን፣ የሲቪል የሽግግር መንግሥት ምሥረታን የሚያስተጓጉሉ ወይም የሚያዘገዩና የሚያደናቅፉ፣ ሐሳብን የመግለጽ ነፃነትን የሚያምቁ፣ በስርቆት የተሳተፉ፣ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የፈጸሙ፣ የተመድን ሰብአዊ እንቅስቃሴ ያስታጉላሉ በተባሉ ግለሰቦች ላይ ፕሬዚዳንቱ ማዕቀብ መጣላቸውን፣ ዋይት ኃውስ በመግለጫው አስታውቋል፡፡

ከሁለት ዓመታት በፊት በሱዳን የተፈጸመው ወታደራዊ ስዒረ መንግሥት እና ከሁለት ሳምንታት በፊት የተጀመረው ትጥቃዊ ግጭት፣ በዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ ደኅንነት እና የውጭ ፖሊሲ ላይ፣ “ያልተለመደ እና ልዩ” ብሎ የገለጸውን አደጋ መጋረጡን፣ ዋይት ኃውስ ጨምሮ አስታውቋል፡፡