ሶማሊያ ውስጥ በወታደራዊ ችሎቶችና በአማፂ ተዋጊ ቡድኖች በዘፈቀደ የሚተላለፉና ተፈፃሚ የሚደረጉ የሞት ፍርዶች ቁጥር በእጅጉ እየጨመረ መምጣት እያሰጋቸው መሆኑን የመብቶች ተሟጋቾች አስታወቁ፡፡
ባለፈው የአራት ወር ተኩል ጊዜ ብቻ ሁለቱም ወገኖች እያንዳንዳቸው ቢያንስ አሥራ ሁለት ግድያዎችን በአደባባይ መፈፀማቸውንና ሁሉም ግድያዎች ሲካሄዱ ከሰላሣ እስከ ሦስት መቶ የሚደርስ ቁጥር ያለው ሰው ቆሞ እንደሚመለከት ተነግሯል፡፡
በፍርድ የሚፈፀሙ የሚመስሉ የዘፈቀደ ግድያዎች ለሶማሊያ አዲስ ባይሆኑም የግድያው ቁጥር እንዲህ ማሻቀብ እንዳሰጋቸው አምነስቲ ኢንተርናሽናልና የአውሮፓ ኅብረት የሶማሊያ ልዑክ አስታውቀዋል፡፡
የአውሮፓ ኅብረቱ ልዑክ በተጨማሪ የሃገሪቱ መንግሥት የሞት ፍርድን እንዲያስቆም ጠይቋል፡፡
በተለይ ባለፈው የአውሮፓ ወር አፕሪል ውስጥ ብቻ በአሥራ አንድ ሶማሊያዊያን ላይ የሞት ፍርድ ያሳለፉት ወታደራዊ ችሎቶች ጉዳዮችን የሥልጣን ገደቦቻቸውን እያለፉ እንደሚመለከቱና ተከሳሾችም በአግባቡ እንዲከላከሉ ሳይደረግ ፍትሕ እንደሚዛባ ተሟጋቾቹ ይናገራሉ፡፡
ባለፈው መጋቢት 30 ከፊል ራስ ገዟ ፑንትላንድ ውስጥ በአደባባይ በጥይት ተደብድበው የተገደሉ አምስት ታዳጊ ወጣቶች የቀረቡባቸው ክሦች ቦሳሶ ከተማ ውስጥ ባለሥልጣናትን ገድላችኋል የሚል ቢሆንም ልጆቹ እንደአዋቂ ለመዳኘት ለሚያበቃ አካለ መጠን ያላደረሱ እንደነበሩ፣ የሕግ ባለሙያ እንዲያነጋግሩ ዕድል እንዳልተሰጣቸውና አጥፍታችኋል የተባሉትን በግድ እንዲያምኑ መደረጋቸውን አምነስቲ ኢንተርናሽናል አመልክቷል፡፡
ልጆቹ የተባለውን ፈፅመናል ያሉት ድብደባ፣ መደፈር፣ የኤሌክትሪክ ንዝረት፣ ብልቶቻቸውን በሲጋራ መጥበስን የመሳሰሉ የማሰቃያ አድራጎቶች ከተፈፀሙባቸው በኋላ መሆኑን የቤተሰቦቻቸውን እማኝነት የጠቀሰው የአምነስቲ ሪፖርት አስታውቋል፡፡
ይህንን የሥቃይ አድራጎት ፈፅመዋል የሚል አቤቱታ የቀረበባቸው ሰዎች ጉዳይ በነፃ አካል እንዲመረመርና አጥፊዎች በተጠያቂነት እንዲያዙ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅ አፍሪካ፣ የአፍሪካ ቀንድና የታላላቅ ኃይቆች አካባቢ ጉዳዮችጽ ምክትል ዳይሬክተር ሚሼል ካጋሪ አሳስበዋል፡፡
የፑንትላንድ ወታደራዊ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ኃላፊ ሳላህ ሊፍ ግን ችሎቱ በግዳጅ እንደማያሳምን ገልፀው የተገደሉት ሰዎችም ዕድሜ በአዋቂነት የሚያስመድባቸው አይደለም የተባለውን አስተባብለዋል፡፡