ሩሲያ የጋዝ አቅርቦቷን ከነገ ጀምሮ እንደምታቋርጥ በማስታወቋ፣ በኃይል እጥረት ስጋት የገባት ሞልዶቫ በከባዱ ክረምት ለሚኖረው የማሞቂያና የመብራት ችግር እየተዘጋጀች ነው፡፡
ለአውሮፓ ኅብረት አባልነት በታጨችው ሞልዶቫ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚቋረጠው ንብረትነቱ የሩሲያ መንግሥት የሆነው ጋዝፕሮም ሀገሪቱ የ709 ሚሊዮን ዶላር ውዝፍ የመብራት ዕዳ አለባት በማለቱ ነው፡፡
የተባለውን የዕዳ መጠን የምዕራባውያን ደጋፊ የኾነችው ሞልዶቫ ውድቅ አድርጋዋለች፡፡ “ሞስኮ የኃይል አቅርቦትን በመሣሪያነት በመጠቀም ሀገሪቱን ለማተራመስ የምትጠቅምበት የፖለቲካ ስልት ነው” በማለትም ከሳለች፡፡
ርምጃው ለአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል ኃይል ያመነጫል ወደ ተባለው በሀገሪቱ ትልቁ ወደ ሆነው ኩሲዩርጋን የኃይል ማመንጫ ጣቢያ የሚለቀቀውን ጋዝ ያስቆማል።
የኃይል ማመንጫው የሚገኘው የሩሲያ ደጋፊዎች ናቸው የተባሉት ተገንጣዮች በሚገኙበት ትራንስኒስትሪያ ክልል መኾኑን የአሶሽየትድ ፕሬስ ዘገባ ይጠቁማል።
እንደ አውሮፓውያን የቀን አቆጣጥር በ1992 በተካሄደ አጭር ጦርነት የተገነጠለችው ትራንስኒስትሪያ በብዙ ሀገሮች ዕውቅና አላገኘችም፡፡
470 ሺሕ ከሚኾኑት ነዋሪዎቿ ብዙዎቹ የሩሲያን ቋንቋ በአፍ መፍቻነት የሚናገሩ ሲኾን ወደ 200 ሺሕ የሚጠጉት የሩሲያ ዜግነት አላቸው፡፡
ትራንስኒስትሪያ በክልሉ የጋዝ አቅርቦት ላይኖር ይችላል በሚል ስጋት በታኅሣሥ ወር መጀመሪያ ላይ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ አውጃለች፡፡
ታዛቢዎች ቀውሱ የሞልዶቫን ሀብት ሊያመነምን፣ ከትራንስኒስትሪያ ጋራ ውጥረት ሊፈጥር እና እ.ኤ.አ በ2025 ከሚካሄደው ምርጫ በፊት የፖለቲካ አለመረጋጋትን ሊያባብስ እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ፡፡
አፍቃሪ ሩሲያ ፓርቲዎች ለኃይል ወጪው መጨመር መንግሥትን ተጠያቂ ያደርጋሉ።
የሞልዶቫ ፕሬዝደንት ማያ ሳንዱ ትላንት ሰኞ በሰጡት መግለጫ “የሩስያ ርምጃዎች ሀገሪቱን ለማተራመስ እና የአውሮፓን ውህደት ለማደናቀፍ ነው” ብለዋል፡፡
የሀገሪቱ የኃይል አቅርቦት በበጋው የሙቀት ወቅት ያልተቋረጠው የኤሌክትሪክ ኃይል በክረምቱም ወራት እንደሚቀጥል ገልጸው፣ ለትራንስኒስትሪያ ነዋሪዎች ሰብአዊ ርዳታ የመስጠት እቅድም መኖሩን ተናግረዋል፡፡
ከዩክሬን ጦርነት በኋላ ለኃይል አቅርቦቷ የሩሲያ ጥገኛ የሆነቸው ሞልዶቫ ከሌሎች የምዕራብ አውሮፓ ሀገራት የኃይል አማራጮችን ለማግኘት ጥረት እያደረገች መሆኑን ተመልክቷል፡፡