የአውሮፓ ፓርላማ በጥብቁ የሰው ሠራሽ የአእምሮ ሕግ ረቂቅ ላይ ድምፅ ሰጠ

ቻትጂፒቲ

የአውሮፓ ኅብረት ሕግ አውጪዎች፣ የጣት አሻራን የመሳሰሉ የባዮሜትሪክ ክትትል መሣሪያ ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን የሚከለክለውን ጨምሮ፣ ከሰው ሠራሽ አእምሮ የመነጩ እንደ ቻት ጂፒት የመሳሰሉት ይዘት አመንጭዎችን በሚያካትተው ጥብቅ የሕግ ረቂቅ ላይ፣ ዛሬ ረቡዕ ድምፅ ሰጥተዋል፡፡

ሕግ አውጭዎቹ፣ የፋብሪካዎችን የምርት እና ሥራ ሒደቶች፣ ከደንበኞች ጋራ የሚደረግ ግንኙነትን፣ በሰው ሠራሽ አእምሮ የመተካትን ሒደት አስመልክቶ በቀረበው ረቂቅ ላይ ተስማምተዋል፡፡ እንዲሁም ሰው አልባ ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ በሁሉም ዘርፍ ያሉትን ቴክኖሎጂዎች አጠቃቀም፣ ወጥ ዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስያዝ፣ በአውሮፓ ኅብረት በቀረበው የሕግ ረቂቅ ላይ እንደተስማሙ ተነግሯል፡፡

ኢላን መስክ እና ሳም ኦልትማንን፣ በማይክሮ ሶፍት የሚደገፈው፣ የኦፕን ኤ አዩ ቻት ጂፒቲ እና ሌሎች ከፍተኛ የሰው ሠራሽ አእምሮ ድርጅት መሪዎች እና ሳይንቲስቶች ጨምሮ ቴክኖሎጂዎቹ በህብረተሰቡ ላይ ሊያስከትሉት ስለሚችሉት አደጋዎች ያላቸውን ስጋት ገልጠዋል፡፡

የሕጉ ረቂቅ ከመጽደቁ በፊት፣ ሕግ አውጭዎቹ፥ ከአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች ጋራ፣ በዝርዝሮቹ ላይ እንደሚወያዩ ተነግሯል፡፡