የኢላን መስክ የቀድሞው ትዊተር፣ የአሁኑ X፣ የማኅበራዊ ሚዲያውን ሕግ ጥሶ እንደሁ ለመወሰን የአውሮፓ ኅብረት ምርመራ በማድረግ ላይ መሆኑን አስታውቋል።
በመረጃ መረብ ላይ የሚለቀቁ መልዕክቶች “መርዛማነታቸው እንዲቀንስ” በሚል ከወጣው ሕግ ወዲህ የተደረገ የመጀመሪያው ምርመራ ነው ተብሏል። መድረኩ የሚጠቀማቸው ሥርዓቶች፣ ቀመሮች እና ፖሊሲዎች ሕግ ጥሰው እንደሁ ይታያል ተብሏል።
መድረኩ ሕገ ወጥ መልዕክቶችን መቆጣጠር ሳይችል ቀርቶ እንደሁ ምርመራው ይመለከታል ተብሏል። በተጨማሪም አሠራሩን በተመለከተ ለተመራማሪዎች እና ለመርማሪዎች ግልጽነት ያሳይ እንደሆነም ይፈተሻል።
X በበኩሉ በለቀቀው መልዕክት፣ ኩባንያው ለሕጉ ተገዢ መሆኑን ጠቅሶ፣ የምርመራ ሂደቱ ከፖለቲካ ነፃ መሆኑና ሃሳብን የመግለጽ ነፃነት መከበር አስፈላጊ እንደሆነ ገልጿል።
“ዲጂታል ሰርቪስ አክት” በሚል የወጣው ሕግ፣ በመጠናቀቅ ላይ ባለው የፈረንጆች ዓመት መጀመሪያ ላይ ተግባራዊ የሆነ ሲሆን፣ ሕጉን በሚጥሱ ኩባንያዎች ላይ የገቢያቸውን 6 በመቶ ድረስ መቀጫ እንደሚጥል ታውቋል። ይህም በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር እንደሚሆን ይገመታል። ቅጣቱ ከአውሮፓ ኅብረት መታገድንም ሊጨምር እንደሚችል ተመልክቷል።