በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የሕክምና ባለሙያዎች በኢትዮጵያ የሕክምና አገልግሎትና ትምህርቱን ይደግፋሉ፡፡
ሰሜን አሜሪካ ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና አሜሪካዊያን የሕክምና ባለሙያዎች በቅርቡ ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ በሚገኘው ሐዋርድ ዩኒቨርሲቲ ተሰብስበው በጤና አጠባበቅና በከፍተኛ ደረጃ ባለው የሕክምና አገልግሎት፣ እንዲሁም በድኅረምረቃ መርኃግብር የኢትዮጵያ አያያዝ ላይ መክረዋል፡፡
በዚህ ሕዝብ ለሕዝብ የሚባል ድርጅት ባዘጋጀው ለሁለተኛ ዓመት በተካሄደ የአንድ ቀን ጉባዔ ላይ እስከ ሰባ የሚደርሱ ሃኪሞች፣ የሕዝብ ጤና አጠባበቅና ሌሎችም ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡
በጉባዔው ላይ ከተገኙት መካከል የሐዋርድ ዩኒቨርሲቲውን የሕዝብ ጤና አጠባበቅ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶ/ር አሕመድ ሞኤን ሐኪሞቹ ወደሃገራቸው እየሄዱ ሕዝባቸውን የማገልገል ኃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
ከጉባዔው አዘጋጆች መካከል የሕዝብ ለሕዝብ የልገሣ ዝግጅትና የምርምር ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሠናይት ከበደ ይገኙበታል፡፡ ዶ/ር ሠናይት በሙያቸው የሕፃናት ሃኪም ናቸው፡፡ በኤችአይቪ/ኤድስ፣ የኢንፍሉዌንዛ ወረርሽኝን ጨምሮ በተለያዩ ወረርሽኞችና የበሽታዎተ መስፋፋት ጉዳይ ላይም ከተለያዩ ዓለምአቀፍ ድርጅቶች ጋር በአማካሪነት ጭምር ይሠራሉ፡፡ በኤምሪ ዩኒቨርሲም የዓለምአቀፍ ጤና ዕድገት መምህር ሆነው ሠርተዋል፡፡
ለዝርዝሩ ዘገባውን ያዳምጡ፡፡