“በክልሉ አምባገነንነት ሰፍኗል፣ ሥጋት ነግሷል። ወጣቶች ከዚያ ለመቆየት የሚያስችል ተሥፋ በማጣታቸው በአደጋ ለተመላ ስደት ተዳርገዋል። መልስ ያልተገኘላቸው ብዙ ጥያቄዎች አሉን።” ዑመር ዶል የድርጅቱ ሊቀ መንበር ናቸው።
“የሕዝባችን ድምጽ ለመሆን ነው፤ ዱልሚ ዲድ የተባለውን ድርጅት አቋቁመናል። ዋና ዓላማችንም በክልሉ የሚታዩትን ችግሮች ይፋ ለማድረግና መፍትሔ ለማግኘት ነው።” ከድር ጅግሬ አደም በንግድ ሥራ የሚተዳደሩት የሜነሶታ ክፍለ ግዛት ነዋሪ የኢትዮጵያ ሶሜሌ ክልል ተወላጅ።
መሰንበቻውን ለዝግጅት ክፍላችን የደረሰ ደብዳቤ ነው መነሻው።በሶማሌ ክልል “በፕሬዝዳንቱና በጥቂት አጋሮቻቸው ተፈጽመዋል” የተባሉ የመብት ጥሰቶች እና “ከሃገር ውጭ የክልሉ ተወላጆች በሚኖሩባቸው አገሮች ጭምር ማስፈራሪያና ዛቻ ይደርስብናል። የዜጎቹን መብት የማስጠበቅ ኃላፊነት ያለበት የፌድራሉም መንግስት ጣልቃ በመግባት እስካሁን ሕዝቡ ለሚያነሳቸው ለእነኚህ የመብት ጥያቄዎች መልስ መስጠት አልቻለም።” የሚሉትን ክሶች ናቸው በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች ደብዳቤ ዝርዝር።
የሕዝባችንን ድምጽ ለማሰማት የመሠረትነው ነው፤ ያሉትን ድርጅት መሪዎችና አንዳንድ አባላት ስርተን እየተንቀሳቀስን ነው፤ ያሉትን ጠያቂዎች አነጋግረናል።
“ዱልሚ ዲድ” .. “የፍትህ ጥያቄ” የሚል ስያሜ ሰጥተውታል።
ዑመር ዶል የድርጅቱ ሊቀ መንበር ናቸው። የሶማሌ ክልል ተወላጅ የሆኑ ኢትዮጵያውያን መናሃሪያ በሆነችው የመካከለኛው ምዕራብ ዩናይትድ ስቴትሷ የሜነሶታ ክፍለ ግዛት ነው የሚኖሩት።
ባለፈው ሕዳር ወር መጨረሻ የተቋቋመው ድርጅታቸው፤ “የክልሉ ፕሬዝዳንት ያለ አንዳች ጠያቂ በሕዝቡ ላይ እያደርሱ ነው” ያሉት በደል እንዲያበቃ ዘላቂ መፍትሔ ፍለጋ የታለመ መሆኑን ይናገራሉ።
“በክልሉ አምባገነንነት ሰፍኗል። ሥጋት ነግሷል። ወጣቶች ከዚያ ለመቆየት የሚያስችል ተሥፋ በማጣታቸው በአደጋ ለተመላ ስደት ተዳርገዋል። መልስ ያልተገኘላቸው ብዙ ጥያቄዎች አሉን።” ይላሉ።
በሜነሶታ ክፍለ ግዛት በንግድ ሥራ የሚተዳደሩት ከድር ጅግሬ አደም ሌላው የድርጅቱ አባል ናቸው።
በተለያዩ ጊዜያት የፌድራል መንግስት ለዚህ ችግር መፍትሄ ያበጅለት ዘንድ የተደረጉ ሙከራዎች እስካሁን ባለመሳካታቸውና የክልል አስተዳደር በሕዝቡ ላይ የሚደርሰው በደል ስላሳሰበኝ በአቶ ዑመር የሚመራው ዱል ሚዲድን ተቀላቀልኩ፣ ይላሉ።
አቶ ከድር እንደ ሊቀመንበሩ ሁሉ እርሳቸውም የክልሉ ሕዝብ ለከፋ ሰብዓዊ መብት ተጋልጧል ባይ ናቸው። ሕገ መንግስታዊ ጥበቃ የሚደረግላቸው መሠረታዊ መብቶች ናቸው የሚጣሱት ሲሉም ከአቶ ዑመር ይስማማሉ።
በተለያዩ አገሮች የሚኖሩት የክልሉ ተወላጅ ኢትዮጵያውያኑ ተሰባስበው ይህን ድርጅት ካቋቋሙ በኋላ ሁኔታዎች መለወጥ መጀመራቸውን የሚናገሩት ሊቀመንበሩ በውጭ አገር የሚኖረውን የብሄረሰቡን አባል ተቃውሞውን ቢገልጽ በቤተሰቡ ላይ አንዳች ጉዳት ሊደርስ እንደሚችል በ’መዛት ሲያስፈራሩት መቆየታቸውን ገልጠው በቅርቡም ተመሳሳይ ዛቻ ደርሶብናል ይላሉ።
በቅርቡም የፕሬዝዳንቱ ረዳቶች ወዲህ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ መጥተው ፈጸሙ ያሉትን አቶ ዑመር ይዘረዝራሉ።
ለበርካታ ዓመታት በዩናይትድ ስቴትስ የኖሩት አቶ ከድር በበኩላቸው “የዚህ ችግር አካል ነው” ያሉትትንና በግል የገጠማቸውን ይናገራሉ።
በዩናይትድ ስቴትስ ከሚያካሂዱት የንግድ ሥራ በተጨማሪ ከዚህ ቀደም ወደ ሃገራቸው በመመለስ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ ጀምረውት የነበረውን የንግድ ሥራ በክልሉ ሰፍኗል ባሉት የመብት ጥሰት እና ሙስና ሳቢያ ለማቋረጥ መገደዳቸውን ነው፤ የገለጡት ።
የለውጥ ጥያቄው በሶማሌ ክልልም ጎልቶ እየተሰማ መሆኑን አክለው የተናገሩት አቶ ከድር የፌድራል መንግስቱ በተጨባጭ የሚወስደውን እርምጃም በቅርበት የሚከታተሉ መሆናቸውን አመልክተዋል።
ከሙስና እስከ ሕገ ወጥ እስርና ግድያ ቁጥሩ የበዛ ውንጀላ የቀረበባቸውን የክልሉን ፕሬዝዳንት አቶ አብዲ ሞሃመድ ዑመርን ምላሽ እየተጠባበቅን ነው። በተጓዳኙ የክልሉን መንግስታዊ የሰብዓዊ መብት ኮምሽን አቶ ጀማል ዋርፋን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት እስካሁን ለጊዜው አልተሳካም። እንደቀናን እናቀርባለን።
ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።
Your browser doesn’t support HTML5