በሶማሊያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሶማሌላንድ ስምምንት ምክንያት ስጋት ላይ ናቸው

  • ቪኦኤ ዜና

ፎቶ ፋይል፦ የባህር በር ስምምነቱን በመቃወም ሶማሊያውያን ህዝባዊ ሰልፍ ወጥተው ሞቃዲሾ፣ ሶማሊያ እእአ ጥር 11/2024

ሶማሌላንድ ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታገኝ የሚረዳትን ስምምነት በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ከፈረመች ወዲህ፣ በሶማሊያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለአካላዊ ጥቃት፣ ዛቻ እና ማስፈራሪያ መጋለጣቸውን፣ በሶማሊያ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ አባላት ለአሜሪካ ድምፅ፣ የሶማሌ ቋንቋ ክፍል አስታውቀዋል።

በአውሮፓውያኑ አዲስ ዓመት ላይ የተፈፀመው ስምምነት፣ በኤደን ባህረሰላጤ ላይ ከሚገኘው በርበራ ወደብ፣ ኢትዮጵያ 20 ኪሎሜትር ርዝመት ያለው የባህር ጠረፍ ለ50 ዓመታት እንድትከራይ እና ለንግድ እና የጦር ሰፈር አገልግሎት እንድትጠቀም የሚፈቅድ ነው። በምትኩ፣ ኢትዮጵያ ለራስ ገዟ ሶማሌላንድ የነፃ ሀገር እውቅና እና ለሶማሌላንድ መንግሥት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርሻ ልትሰጥ እንደምትችል ስምምነቱ ያመለክታል።

ስምምነቱ ሶማሌላንድን እንደ ግዛቷ አካል አድርጎ ከሚመለከተው የሶማሊያ መንግሥት ከፍተኛ ትችት አስነስቷል። ሞቃዲሾ ስምምቱ "የወረራ ድርጊት ነው" በማለት፣ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት እንደሚያስጠብቅ ቃል ገብቷል። በሶማሌላንድም ስምምንቱን የሚደግፉ እና የሚቃወሙ ሰልፎች ተካሂደዋል።

የአልሻባብ ታጣቂዎችም በቃል አቀባያቸው አሊ ሞሐመድ ራጅ በኩል ስምምነቱን አጥብቀው ያወገዙ ሲሆን፣ ምናልባትም የሶማሊያ ብሄራዊ ስሜት በማሳየት ድጋፍ ለማሰባሰብ እየተጠቀሙበት ሊሆን እንደሚችል ተዘግቧል።

ሰኞ እለት በደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ በምትገኘው ቤሌድ ሐዎ ከተማ የአልሻባብ ታጣቂዎች በለሊት በፈፀሙት ጥቃት ከተገደሉት ሰዎች መካከል ስድስቱ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን የከተማዋ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

በከተማዋ የሚገኝ አንድ ወረዳ ኮሚሽነር የሆኑት አብዲራሺድ አብዲ አሮግ ለአሜሪካ ድምፅ የሶማሌ ቋንቋ አገልግሎት እንደገለፁት፣ ታጣቂዎቹ አንድ መኖሪያ ቤት ላይ ጥቃት አድርሰው አምስት ሴቶችን እና ሁለት ወንዶችን ገድለዋል። ከነዚህ ውስጥ ስድስቱ የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ ሰባተኛዋ የሶማሊያ ተወላጅ መሆኗን ገልፀዋል። ሌሎች ስድስት ኢትዮጵያውያንም በጥቃቱ መጎዳታቸውን አመልክተዋል።

ጸረ-ኢትዮጵያዊ ስሜት በሶማሊያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን እና ፍልሰተኞችንም እየጎዳ ነው። በሶማልያ በምትገኘው ቦሳሶ ከተማ ውስጥ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ስደተኛ አብዲ ቡሮው ለአሜሪካ ድምፅ ሲያስረዳ "እስካሁን ድረስ አካላዊ ጥቃት አላየንም። ነገር ግን የቃላት ዛቻ የፈጠረው ውጥረት አለ። የሚያስፈራሩን ሰዎች ሁሌም፣ ኢትዮጵያ በጉልበት የሶማሊያን መሬት ልትወስድ ስለፈለገች በግዳጅ ወደ ኢትዮጵያ ትባረራላችሁ ይሉናል" ብሏል።

የ40 ዓመቷ ሳኪና ኤደንም ኢትዮጵያዊ ስደተኛ ስትሆን ቦሳሶ ውስጥ ቡና በመሸጥ ትተዳደራለች። ባለቤቷ ከዓመት በፊት መሞቱን የምትገልፀው ሳኪና፣ በአወዛጋቢው ስምምንት ምክንያት ስጋት ውስጥ መውደቋን ታስረዳለች። "ደንበኞቼ ስለኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ ስምምነት ሲወያዩ አንዳንዶቹ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በሶማሌላንድ ላይ ባላቸው ፖሊሲ በመናደዳቸው ከዚህ በኃላ የኔን ቡና እንደማይገዙ ነግረውኛል" ብላለች።

በኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ የደህንነት ስጋት ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ አንዳንድ ምሁራን እና የማኅበረሰቡ አባላት የስደተኞቹን መብት በመደገፍ ድምፃቸውን እያሰሙ ነው። ከነዚህ መካከል አንዱ ሙስጣፌ ዩሱፍ የህግ ባለሙያ ሲሆን "እነዚህ ስደተኞች፣ በነፃነት መንቀሳቀስ፣ ጥበቃ ማግኘት፣ ትምህርት እና ጤናን ጨምሮ መሰረታዊ መብታቸውን መጠቀም መቻል አለባቸው። በፖለቲካ ምክንያት ሊገለሉ ወይም ተፅእኖ ሊደርስባቸው አይገባም" ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

ሀያት ሞሐሙድ አብዲ የተባለች ሌላ የሶማሊ ምሁርም፣ ንፁሃን ስደተኞች በፖለቲካ ምክንያት ዒላማ ሊደረጉ አይገባም ትላለች።

"ሶማሊያውያን በዓለም ዙሪያ ስደተኛ ነበሩ፣ አሁንም ናቸው። እንደሚመስለኝ በሶማሊያ የሚገኙ ሶማሊዎች ኢትዮጵያዊ እንግዶቻቸውን ልክ እንደ ሶማሊዎች ሊያስተናግዷቸው ይገባል። የኢትዮጵያ ስደተኞችም በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል በተፈጠረው የባህር ወደብ ውዝግብ ውስጥ መግባት የለባቸውም።"

በሶማሊያ የሚኖሩት፣ በአብዛኛው የኦሮሞ ተወላጆች የሆኑት ኢትዮጵያውያን ወደ ፑንትላንድ እና ሶማሌላንድ የሚሄዱት ቀይ ባህር ለመድረስ ስለሚያመቻቸው ነው። አብዛኞቹ ስደተኞች ዓላማቸው የተሻለ ህይወት ለማግኘት ወደ አረብ ባህረሰላጤ ማምራት ቢሆንም፣ ብዙዎቹ በገንዘብ ችግር፣ የጉዞ ክልከላዎች እና በየመን ባለው ጦርነት ምክንያት ተስፋ ቆርጠው በሶማሌላንድ እና ከፑንትላንድ ቀርተዋል።