"የሉዓላዊነት ቀን" በሚል በመላው አገሪቱ ከተከናወኑት መርሃ-ግብሮች በአንዱ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ "በኛ በኩል ምንም አይነት የጦርነት፣ የግጭት ፍላጎት የለንም" ሲሉ አክለዋል።
ኢትዮጵያ ታኅሳስ 22 ቀን 2016 ዓ/ም ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችውን የመግባቢያ ስምምነት ተከትሎ፣ ከሶማሊያ ጋር ያለው ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ በቀጠለበት ወቅት የተደረገው የጠቅላይ ሚንስትሩ ንግግር የትኛውንም አገር በስም አልጠቀሰም።
የሶማሊያ መሪዎች በተለያያ ጊዜ በሰጧቸው አስተያየቶች፣ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር አወዛጋቢውን ውል በመፈራረም ሉአላዊነታችንን ተዳፍራለች በማለት ከሰዋል። "የቆዩ ግጭቶችን እየቀሰቀሰች ነው" በሚል ኢትዮጵያን መወንጀላቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ በዛሬው ንግግር የሶማሊያን ስም በቀጥታ አላነሱም። "ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ ከአንዳንድ አገራት ጋር ግጭት ልትገባ እንደምትችል የሚነገሩ ንግግሮች አሉ" ያሉት የኢትዮጵያው የጠቅላይ ሚንስትር ባለፉት ሃምሳ አመታት ኢትዮጵያ ከሱዳንና ከሶማሊያ ጋር ግጭት ውስጥ ገብታ እንደነበርም አስታውሰዋል።
እሳቸው በሥልጣን ላይ የቆዩባቸውን ያለፉትን ስድስት አመታት ተኩል በመጥቀስ ግን "በአንድም ጎረቤት ላይ አንድም ጥይት ተኩሰን አናውቅም" ብለዋል። "ከማንም ጋር የመጋጨት ፍላጎት፣ አላማም ሆነ ሃሳብ የለንም" በማለትም አክለዋል።
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋራ የተፈራረመችውን የመግባቢያ ሰነድ ተከትሎ ባለፈው ታህሳስ የተቀሰቀሰው የአዲስ አበባ እና የሞቃዲሾ የዲፕሎማሲ ውዝግብ እስካሁን መቋጫ ሳያገኝ ቀጥሏል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ አምስት ሀገራት ወታደሮችን ያዋጡበትን ነባሩን የአፍሪካ ሕብረት የሶማሊያ የሽግግር ተልዕኮ - አትሚስ’ን በመተካት፣ እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ2025 ስምሪት ይቀበላል’ በተባለው አዲሱ በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት ድጋፍ እና የማረጋጋት ተልዕኮ ውስጥ የኢትዮጵያን መካተት እንደማትፈልግ ሶማሊያ መግለጿም ይታወቃል፡፡ በዓባይ ውሃ ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋራ አለመግባባት ውስጥ ከምትገኘው ከግብፅ ጋራ የመከላከያ ሥምምነት መፈራረሟም ይታወሳል።
በሌላ በኩል ግብፅ በአዲሱ የአፍሪካ ሕብረት ተልዕኮ ሚና እንዲኖራት እንደምትፈልግም ሶማሊያ ጠቁማለች። ኢትዮጵያ በበኩሏ ‘ሶማሊያ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጻረሩ ኃይሎችን ከማስተናገድ እንድትቆጠብ’ ስትል አሳስባለች። "ሌሎች ተዋናዮች የአፍሪካ ቀንድ ክልልን ለማተራመስ እርምጃ ሲወስዱ ኢትዮጵያ በዝምታ አትመለከትም” ሲል ባለፈው ሳምንት ይፋ የተደረገው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ማመልከቱ ይታወሳል።