ቅዱስ ሲኖዶስ “ቀኖና ጣሾች” ባላቸው ሊቃነ ጳጳሳት እና መነኰሳት ላይ ያሳለፈውን ውግዘት አነሣ

Your browser doesn’t support HTML5

ቅዱስ ሲኖዶስ “ቀኖና ጣሾች” ባላቸው ሊቃነ ጳጳሳት እና መነኰሳት ላይ ያሳለፈውን ውግዘት አነሣ

· ቀሪዎቹ አምስት መነኰሳት እንዲመለሱ በድጋሚ አሳስቧል

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ፣ ቀኖና እና አስተዳደራዊ መዋቅር በመጣስ፣ “የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ሰጥተዋል፤” በሚል በቅዱስ ሲኖዶስ ቃለ ውግዘት ተላልፎባቸው የነበሩ ሊቃነ ጳጳሳት እና መነኰሳት፣ ዛሬ በተካሔደው የቅዱስ ሲኖዶሱ ጉባኤ፣ ውግዘቱ እንደተነሣላቸው ቤተ ክርስቲያኗ አስታወቀች፡፡

ለአሜሪካ ድምፅ መረጃውን የሰጠው የቤተ ክርስቲያኗ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ እንደገለጸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና አቶ ሽመልስ አብዲሳ በተገኙበት፣ ሕገ ወጥ ሹመቱን ከሰጡት ሦስቱ ሊቃነ ጳጳሳት ጋራ ስምምነት በተደረሰባቸው ዐሥሩ ነጥቦች መሠረት፣ ቅዱስ ሲኖዶስ በስፋት ከተወያየ በኋላ፣ የተላለፈባቸው ቃለ ውግዘት ከዛሬ መጋቢት 21 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ተነሥቶላቸዋል፡፡

በመኾኑም፣ ሦስቱም አባቶች፣ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ፣ ብፁዕ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ እና ብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስ፣ በቀድሞው የሊቀ ጳጳስነት ማዕርጋቸው ይጠራሉ፤ አስቀድመው ተመድበው ይሠሩባቸው በነበሩት አህጉረ ስብከት ሥራቸውን ይቀጥላሉ፡፡

በተመሳሳይ ኹኔታ፣ ለስምምነቱ ተገዥ በመኾን፣ በጽሐፍ ጥያቄአቸውን ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ያቀረቡት 20 የቀድሞ መነኰሳትም፣ ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም. በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የተላለፈባቸው ውግዘት፣ ከዛሬ መጋቢት 21 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ እንደተነሣ በውሳኔው ተጠቅሷል፡፡ ቀሪዎቹ አምስቱ ግን፣ በአለው ጊዜ ተጠቅመው ወደ ቤተ ክርስቲያናቸው እንዲመለሱ ያሳሰበው ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ ውግዘቱን በሚመለከት በቋሚ ሲኖዶስ በኩል ታይቶ እንዲፈጸም ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡ በመኾኑም፣ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት፣ 20ዎቹ መነኰሳት፣ ከዲቁና እስከ ቁምስና ባለው ማዕርገ ክህነታቸው እንዲያገለግሉና በምንኵስና ስማቸውም እንዲጠሩ ቅዱስ ሲኖዶሱ ወስኗል፡፡ የታገደባቸው ደመወዝ እና ጥቅማጥቅም ተሰልቶ እንደሚሰጣቸው፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ሓላፊ ሊቀ ትጉሃን እስክንድር ገብረ ክርስቶስ ለአሜሪካ ድምፅ ገልጸዋል፡፡

ሹመቱን በመቃወም ተፈጥሮ በነበረው ችግር፣ ያጋጠመውን የሕይወት መጥፋት፣ አካል ጉዳት፣ እስራት፣ የመብቶች ጥሰት እና ንብረት ውድመት በተመለከተም፣ ቤተ ክርስቲያን ጉዳዩን በሕግ እንደያዘችው ታውቋል፡፡

ይኹን እንጂ፣ ከቀኖና ውጭ ተሾመው ነበር የተባሉት መነኰሳት፣ በቅዱስ ሲኖዶሱ የወጣውን የመመዘኛ መስፈርት ከአሟሉ፣ በመጪው ግንቦት ወር እንደሚካሔድ በሚጠበቀው የኤጲስ ቆጶሳት መረጣ እና ሹመት ተሳታፊ ይኾናሉ፤ ብለዋል፡፡ ምእመናንም፣ የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔ እንዲያከብሩ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

ከሹመቱ ጋራ ተያይዞ በተቀሰቀሰው ግጭት፥ የሞቱትን፣ የአካል ጉዳት የደረሰባቸውን፣ የታሰሩትን፣ የመብቶች ጥሰት የተፈጸመባቸውን ጨምሮ በንብረት ላይ የደረሰውን ውድመት በተመለከተ ቤተ ክርስቲያኒቱ በሕግ እየተከታተለች እንደ ኾነ አብራርተዋል፡፡

በወሎ ዩኒቨርሲቲ መምህር የኾኑት ቀሲስ ዶክተር ይቻለዋል ጎሽሜ በቅዱስ ሲኖዶሱ የተሰጠው ውሳኔ፣ “የቤተ ክርስቲያኗን ህልውና የሚያጸና፣ የምእመኑንም አንድነት የሚያጠናክር ነው፤” ብለውታል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቴሌቪዥን፣ ከአንድ ቀን በፊት ይፋ በአደረገው መረጃ፣ ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም. በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሀሮ ዳጩ በዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ፣ ሕገ ወጥ ባለው መንገድ ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት ተፈጽሞላቸዋል ከተባሉት መሀከል 18ቱ፣ የይቅርታ ደብዳቤ ማስገባታቸውን አስታውቆ ነበር፡፡

የይቅርታ ደብዳቤ አስገብተዋል፣ ውግዘቱም ተነሥቶላቸዋል ከተባሉት አንዱ የኾኑትን ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስን፣ በእጅ ስልካቸው ላይ አግኝተን ለማነጋገር ብንሞክርም፣ “ከአካባቢው ወጣ ስላልኹኝ ስለ ጉዳዩ የማውቀው ነገር የለም፤” የሚል ምላሽ ሰጥተውናል፡፡