ዘካሪያስ ጥበቡ የኢትዮጵያን ምድር ለቆ በሰሃራ በረሃ በኩል እስራኤል ለመግባት የእግር ጉዞ ሲጀምር ራሱን ከኑሮ ሸክም ከማላቀቅ የተለየ ምክኒያት አልነበረውም። አባቱ በደርግ ዘመን ባለሥልጣን ነበሩ። ከእናቱ ጋር የተዋወቁት አስመራ ከተማ ነው። "አባቴ ወደ ድሬደዋ ሲዛወር እናቴን ይዟት መጣና እኔና ወንድሜ ድሬደዋ ተወለድን" ይላል ዘካሪያስ ታሪኩን ደኋላ ተመልሶ ሲተርክ።
Your browser doesn’t support HTML5
ዘካሪያስ ዕድለኛ አልነበረም ከቤተሰቡ ጋር የማደግ ዕድል አላጋጠመውም የሰባት ዓመት ልጅ እያለ አባቱ ሥራ ብሎ ሄዶ በዛው ሳይመለስ ቀረ። እናቱ ሐዘኑን አልቻለችውም። ሌላ ሐዘን ተደገመ ወንድሙ ታሞ ሕይወቱ አለፈ። "ከዛ እናቴ እኔን ይዛኝ ወደ አባቴ ሀገር ጎንደር ሄደች። እዛ ትምሕርትና ሥራ ጀመርኩ። እሷም አንዳንድ ነገር መሥራት ጀመረች ግን ብዙም ሳንቆይ ወደ አዲስ አበባ ሄድን። ከዛ ደግሞ ወደ ሽሬ .... እናቴ ግን ብዙ አልቆየችም ታማ ሕይወቷ አለፈ። እኔ ከአክስቴ ጋር ኑሮ ጀመርኩ ግን በጣም ኃይለኛ ስለነበረች መስማማት አልቻልንም... በቃ ሀገር ለቅቄ ወጣሁ።"
ዘካሪያስ የቤተሰብ እጦትና ሥራ ማጣት ከፊቱ ተጋረጡበት። ጎንደር እያለ ፀጉር ቤት ውስጥ ይሠራ ነበርና እዛ ከእስራኤል የሚመጡት ደንበኞች ያላቸውን የገንዘብ ነፃነት ይመለከት ስለነበር ልቡን ለጉዞ አነሳሳ። እስራኤል ገብቶ ያሰበውን ገንዘብ ለማግኘት ጉዞውን በእግሩ ጀመረ። "በበሱዳን፣ በግብፅና በእስራአኤል ድንበር እንዲሁ በሲና በረሃ ያሳለፍኩት ስቃይና መከራ ከሕሊና የሚፋቅ አይደለም። ብዙ ጓደኞቼን አጣሁበት። ብዙ እህቶቼ ፊት ለፊቴ ዐይኔ እያየ ተደፈሩ። ወንድሞቼም እንዲሁ በርሃብና በውሃ ጥም ሞቱ።"
ዘካሪያስ በዚህ ጉዞው እስራኤል ድንበር ላይ በግብፆች ተይዞ ሁለት ዓመት መታሰሩን ይናገራል። በጉዞው አብረው ከነበሩት ከ1ሺሕ በላይ ስደተኞች በሕይወት ተርፈው የገቡት ከ42 እንደማይበልጡ ይገልፃል። በመጨረሻ ካናዳ ሲደርስ ሦስት እጅግ አሰቃቂ ዓመታትን አሳልፏል።
ሰውመሆን ይስማው የፊልሙ ጹሑፍና አዘጋጅ ሰውመሆን ነው። የቀረጸውም እርሱ ነው። ሰውመሆን በሞያ አጋራቹ እና ወዳጆቹ ዘንግ ሶሚክ በሚለው መጠሪያ ይታወቃል። በርካታ የፊልም ሥራዎችን ሠርቷል። "የዘካሪያስ ስደት የጀመረው እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ከአንዱ ሀገር አንዱ ሀገር በመሆኑ ታሪኩን ስንከተል ለቀረፃው ብዙ ቦታን ረግጠናል" ይላል።
"በኑሮዬ ደስተኛ ነኝ" የሚለው ዘካሪያስ አሁን በካናዳ ናርዶስ ከተባለች ባለቤቱ ጋር ሁለት ልጆች አፍርተዋል። የፊልሙን የመጀመሪያ ታሪክ የጻፈውና ታሪኩን የተጫወተው እራሱ ነው። ፕሮዲዩስ ያደረጉት ደግሞ ከባለቤቱ ጋር በጋራ በመሆን ነው።
"ይህን ታሪክ ለመሥራት የፈለኩት አሁንም ድረስ በየቀኑ በምሰማው የስደት ታሪክ ሕሊናዬ እየተረበሸ ተቸገርኩ። ምናልባት አንድ ሰው እንኳን ማስተማር ከቻልኩ እኔም የበኩሌን ላድርግ ብዬ ነው" የሚለው ዘካሪያስ "እንዲህም ሆኖ ግን ያለፍኩበት ስቃይ ሕሊናዬን መረበሹን መቼ እንደሚያቆም አላውቅም" ይላል።
Your browser doesn’t support HTML5
"ዕውር አሞራ ቀላቢ" በኒዩርክ የአፍሪካ ፊልም ፌስቲቫል ላይ ከጠንካራ ፊልሞች አንዱ ወይም “Centerpiece ” ሆኖ ለመታየት ተመርጧል። እንዲሁም በዳላስ ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫል ላይ ለእይታ ይበቃል።