የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ በረራን ሊጀምር ነው

  • ቪኦኤ ዜና
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኞች በአዲስ አበባ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በቦይንግ 737 ማክስ ፊት ለፊት የቡድን ፎቶ ሲነሱ እአአ ፌብሩዋሪ 1 ቀን 2022

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኞች በአዲስ አበባ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በቦይንግ 737 ማክስ ፊት ለፊት የቡድን ፎቶ ሲነሱ እአአ ፌብሩዋሪ 1 ቀን 2022

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ የተባለውን አውሮፕላን እንደገና ለበረራ አገልግሎት ዝግጁ ለማድረግ ማቀዱን አስታውቋል፡፡

ይሁን እንጂ የዛሬ ሦስት ዓመት አካባቢ ከደረሰው አደጋ ወዲህ አየር መንገዱ አውሮፕላኑን ለመጀመሪያ ጊዜ ለበረራ ስለመጠቀሙ ጥያቄዎች መነሳታቸው ተመልክቷል፡፡

እኤአ መጋቢት 2019 ከአዲስ አበባ ከተነሳ ሦስት ደቂቃዎች በኋላ 157 መንገደኞችና የበረራ ሠራተኞችን እንደጫነ የተከሰከሰው የቦይንግ ማክስ 737 አውሮፕላን ከዚያም አምስት ወራት ቀደም ብሎ ኢንዶኔዥያ ላይ በደረሰበት ተመሳሳይ አደጋ 189 መንገደኞችን ይዞ መውደቁ ተጠቅሷል፡፡

በዚህ የተነሳም ከተለያዩ የዓለም የበረራ መስመሮች ታግዶ እንዲቆይ የተደረገ መሆኑም ተገልጿል፡፡

አደጋው ቦይንግን እስከ 20 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ ያደረሰበት መሆኑ ሲገለጽ በርካታ የቴክኒክ የደኅንነት ጥያቄዎችን በወቅቱ ማስነሳቱም ተመልክቷል፡፡

አየር መንገዱ በሰጠው መግለጫ ጋዜጠኞችን ዲፕሎማቶችና ባለሥልጣናቱን ጨምሮ በአፍሪካ ትልቁ ተራራ ወደ ሆነው የኪሎ ማንጆራ ተራራ አድርጎ በመብረር ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ የናሙና በረራ ማቀዱን አስታውቋል፡፡

አየር መንገዱ እኤአ ጥር 22 በሰጠው መግለጫ ከዚህ ውሳኔ የደረሰው የተለያዩ ተቆጣጣሪ ባለሙያዎችን በተደጋገመ ክትትልና ቁጥጥር ማረጋጋጫ ካገኘ በኋላ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገ/ማርያም የአውሮፕላኖቹን ስሪትና የማሻሻያ ሥራዎች ከ20 ወራት በላይ ለሚሆን ጊዜ ተፈትሾ የተረጋገጠ ሲሆን አስተማማኝ ደህንነቱ በአብራሪዎቻችን፣ በኢንጂነሮችና የበረራ ቴክኒሻኖቻችን በሙሉ የተረጋጋጠ ነው ማለታቸው በኦስሼይትድ ፕሬስ ተጠቅሷል፡፡

ዘገባዎቹ የአሶሼይትድ ፕሬስ እና የዳዊት እንደሻው ናቸው፡፡