የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ መረጃ ማጣሪያ መግለጫ

የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ መረጃ ማጣሪያ ዛሬ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግሥት እያካሄደ ነው ላለው ሕግ የማስከበር ዘመቻ የተሳሳተ ትርጓሜ እየተሰጠ መሆኑን በመግለፅ በተሳሳተ ሁኔታ ተተርጉመዋል ያላቸውን ነጥቦች አብራርቷል።

“ኢትዮጵያ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት እየገባች ነው በሚል እየተገለፀ ያለው ፍፁም የተሳሳተ ነው” በማለት ባብራራበት ክፍል በኢትዮጵያ የተጀመረው ሕግ የማስከበር ዘመቻ ዓላማ በግልጽ የተቀመጠና እርሱም የሕወሓትን ወንጀለኛ ቡድን ለሕግ ማቅረብ ነው። ይህ ዘመቻም መጠናቀቂያው ላይ ደርሷል ይላል።

ሌላው ማብራሪያ የሰጠበት ጉዳይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መቀሌን እና ሌሎች የትግራይ ከተሞችን በቦምብ እየደበደበ ነው እንዲሁም“መቀሌ ውስጥ በሚደረግ ዘመቻ ምንም ምሕረት አይኖርም” ተብሏል እና ሲቪሎች እየተገደሉ ነው በሚል በሕወሓት ቡድኖች በተደጋጋሚ የሚተላለፈው መረጃ የፈጠራ ወሬ ነው ብሎታል።

አስከትሎም መንግስት እየወሰደ ባለው ሕግ የማስከበር እርምጃ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሲቪሎች የጥቃት ሰለባ እንዳይሆኑ እጅግ ከፍተኛ ጥንቃቄ እያደረገ ነው ነው ብሏል የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ መረጃ ማጣሪያው። ሆስፒታሎች፣ትምህርት ቤቶች እና የመኖሪያ ቦታዎች ላይ ምንም ዓይነት የጥቃት እርምጃ አይወሰድም ሲልም አስታውቋል።