የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሚቲኦሮሎጂ ኤጀንሲ ዓለምአቀፍ ደረጃዎችን በጠበቁ መሣሪያዎች፣ መረጃ አሰባሰብ፣ አሠረጫጨትና አከመቻቸት የሚንቀሣቀስ ድርጅት መሆኑን የድርጅቱ ተ/ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ዱላ ሻንቆ አስታወቁ፡፡
ኤጀንሲው የዓለም የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት አባል መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልፀው ከ11 የዞን ፅ/ቤቱ አንድ ሺህ በሚሆኑ ሠራተኞቹ ጭምር የሚያሰባስባቸውንና የሚያደራጃቸውን የቅኝት መረጃዎች ያለፖለቲካና ሌላም ጫና ለሃገሮች በነፃ እንደሚያካፍል አመልክተዋል፡፡
በአደረጃጀቱ በአፍሪካ የላቀ መሆኑን የገለፁት አቶ ዱላ ሻንቆ የኢትዮጵያ ሚቲኦሮሎጂ ኤጀንሲ በዌብ ሣይት ጭምር መረጃውን እንደሚበትንና ተቀባይነትና ተዓማኒነት ያለው መረጃ ለኢንሹራንስ፣ ለጤና፣ ለግብርና፣ ለመንገድ ግንባታ፣ ለሲቪል አቪየሽንና ለሌሎችም በርካታ ተቋማትና ጉዳዮች አገልግሎት ላይ እንደሚውል ተናግረዋል፡፡
"መረጃ ለዓለም መስጠት የምንችለው ከዓለም ጋር ስንሄድ ነው፤ ስለዚህ ኅብረተሰባችን ከዓለም ጋር እንደምንሠራ አውቆ በሙሉ ዕምነት የእኛን መረጃ እንዲጠቀም እንጠይቃለን፡፡" ብለዋል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሚቲኦሮሎጂ ኤጀንሲ ተ/ም/ዋና ዳይሬክተር፤ አቶ ዱላ ሻንቆ፡፡
ከየትኛውም አደጋ ለኢትዮጵያ እጅግ የከፋ ጠላቷ የሆነው ድርቅ በዚህ ዓመት እንደማይከሰት አቶ ዱላ ትንበያዎቹን መሠረት አድርገው ተናግረዋል፡፡