የራጅ ሻህ የኢትዮጵያ ጉብኝትና የዩኤስኤአይዲ አዲስ ልገሣ

የዩናይትድ ስቴትስ የዓለምአቀፍ ልማት ኤጀንሲ ዋና አስተዳዳሪ ራጅ ሻህ ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሲሰጡ

ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚካሄዱ የተጨማሪ ምግብ አቅርቦትና የድርቅ ጉዳት ማስወገጃ መርኃግብሮች ዩናይትድ ስቴትስ የ127 ሚሊየን ዶላር ተጨማሪ ድጋፍ መመደቧን አስታወቀች፡፡

የአሜሪካን አዲስ ድጋፍ ይፋ ያደረጉት በምሥራቅ አፍሪካ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት የዩናይትድ ስቴትስ የዓለምአቀፍ ልማት ድርጅቱ ዋና አስተዳዳሪ ዶ/ር ራጅ ሻህ ናቸው፡፡

ድርቁ አብዝቶ ባጠቃው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት የአሜሪካው የዓለምአቀፍ ልማት ተቋም - ዩኤስኤአይዲ ኃላፊ ዶ/ር ራጅ ሻህ ዛሬ ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል፡፡

የንግግራቸው ማዕከላዊ ነጥብ በምሥራቅ አፍሪካ ቁጥሩ በውል ተለይቶ ለማይነገር ሕይወት መጥፋት ሰበብ የሆኑ ድርቆችና ተያይዟቸውም የሚከሰተው የበረታ የምግብ እጥረት ችግርና ቀለበት ሊሰበርና ለአካባዊ ዘላቂ መፍትሔ ማግኘት የሚቻልበት መንገድ እንደነበረ ታውቋል፡፡

ዶ/ር ሻህ በዚህ ጉብኝታቸው ሦስት አዳዲስ የዕርዳታ መድብሎችን ይዘው የተጓዙ ሲሆን አንደኛው ሥር በሰደደና በተራዘመ ረሃብ የሚሰቃዩ 1 ሚሊየን ተኩል ሕፃናትን ለመድረስ ለሚያስችል የምግብ ዋስትና መርኃግብር ማስፋፊያ የሚውል የ110 ሚሊየን ዶላር ወጭ ነው፡፡

በአካባቢው በምግብ እጥረት ችግር ውስጥ ከሚገኘው 12 ነጥብ 4 ሚሊየን አብዛኛው ሰው የሚገኘው በአፍሪካ በሕዝቧ ብዛት ሁለተኛ በሆነችው ኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑ ተዘግቧል፡፡

ዝርዝሩን ከዘገባው ያዳምጡ፡፡