በሶማሊያ አዲሱ የአፍሪካ ህብረት ተልእኮ ሽግግር ስጋት ነው - ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ መንግስት በመጪው ዓመት መጀመሪያ ላይ በሶማሊያ ስራ እንዲጀምር የታቀደው አዲሱ የአፍሪካ ህብረት ተልእኮው ሽግግር “ቀጠናውን ለስጋት የሚያጋልጥ ነው” ብሏል።

የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አዲሱን ተልእኮ ደግፈዋል፡፡

በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ ወይም በምህጻሩ አውሶም (AUSSOM) በመባል የሚታወቀው አዲስ ተልእኮ በዓመቱ መጨረሻ ስምሪቱ ከሚያበቃው ከአሁኑ የአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ የሽግግር ተልዕኮ ወይም አትሚስ (ATMIS) ስምሪቱን ይቀበላል፡፡

ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ቡሩንዲ እና ጅቡቲ አሁን ላለው ተልዕኮ ወታደሮቻቸውን ያዋጡ ቢሆንም ሶማሊያ በአውሶም ተልዕኮ ውስጥ የትኞቹን ሀገራት እንደሚመርጡ ገልፃ አዲስ አበባ የፈረመችውን አወዛጋቢ የመግባቢያ ስምምነት እስካልሻረች ድረስ ኢትዮጵያን እንደምታገል ዝታለች፡፡

ከሁለት ሳምንት በፊት ሶማሊያ ከግብፅ ጋር የመከላከያ ስምምነት ተፈራርማለች፡፡ የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አህመድ ሙአሊም ፊቂ "ፀረ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የሚደረገውን ጥረት ለማጎልበት ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደሚያበረክት እና በተጨማሪም የመከላከያ ሰራዊታችንና ሃይላችንን በብቃት ለመጠበቅ ያለውን አቅም በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል" ብለዋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ሁለት የሶማሊያ ምንጮች እንደገለጹት ባለፈው ማክሰኞ ሁለት የግብፅ ወታደራዊ አውሮፕላኖች ወታደራዊ ትጥቅ ጭነው ሞቃዲሾ ደርሰዋል።

ኢትዮጵያ አዲሱን ተልዕኮ የማዘጋጀት ኃላፊነት ያለባቸው አካላት "የቀጠናው ሀገራት እና ሠራዊት የሚያዋጡ ሀገሮች ህጋዊ ስጋቶች ግምት ውስጥ ማስገባት አለባቸው" ትላለች።

ኢትዮጵያ በመግለጫው ለሽግግሩ ዝግጅት እየተካሄደ ባለበት ወቅት ክልሉ “ወደ ማይታወቅ አደጋ እየገባ ነው” ብላለች።

በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል የወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ “ሌሎች ተዋናዮች አካባቢውን የሚያተራምስ እርምጃ ሲያራምዱ በዝምታ አትመለከትም” ያለ ሲሆን፥ ክልላዊ እና አለማቀፍ የሽብር ሃይሎች ላይ የተገኘውን ድል አደጋ ላይ የሚጥል እንቅስቃሴን በፍጹም አንታገስም” ብሏል።

ሶማሊያ እንደ ግብፅ ካሉ የውጭ አካላት ጋር ትተባበራለች ስትል ኢትዮጵያ በቀጠናው የከፈለችው መስዋዕትነት እየተበላሸ ነው መሆኑን አስታውቃለች፡፡

ሶማሊያም በተለይ ከሶማሌላንድ ጋር የተደረገው አወዛጋቢ የመግባቢያ ስምምነት እስካልተሻረ ድረስ የኢትዮጵያ ጦር በተልዕኮው እንዲሳተፍ የማትፈቅድ መሆኑን አስታውቃለች፡፡

ሶማሊያ ግብጽ የተልእኮው አባል እንድትሆን ትፈልጋለች፡፡

ሶማሊያ “በሽግግሩ ተሳታፊዎችን በመምረጥ የራሷን ተጽኖ ማኖር ትፈልጋለች” የምትለው ኢትዮጵያ ይህ ቀጣናውን አለመረጋጋት እንደሚያሳጣው አስጠንቅቃለች።

በቱርክ ኢትዮጵያና ሶማልያን ለማቀራረብ የሽምግልና ጥረቶች ቢደረጉም አለመግባባቱ አሁንም አልተፈታም፡፡

በዚህ ያልተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ኢትዮጵያ በአዲሱ አውሶም (AUSSOM) ተልእኮ ውስጥ ያላት ተሳትፎ ምን እንደሚሆን አልታወቀም፡፡

አዲሱ ተልእኮ ወይም አውሶም (AUSSOM) 11,900 ሰራተኞችን በመያዝ በሶማሊያ ለሶስት አመታት ይሰማራል ተብሎ ይጠበቃል።