ክሥና መልስ በሶማሌ ክልል መንግሥት ላይ

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ውስጥ የፖለቲካና የምጣኔ ኃብት ጭቆናዎች ይደረጋሉ፤ የእንቅስቃሴ ነፃነትም የተገደበ ነው ሲሉ አንድ የክልሉ ምክር ቤት አባል ለቪኦኤ ገልፀዋል።በሌላ በኩል ግን ክልሉ እየለማ ያለበት ሰላም የሠፈነበትና አስተዳደሩም መልካም ነው ሲሉ አንድ የክልሉ ፕሬዚዳንት አማካሪ ተናግረዋል።

አሊ ጌዲ በሚል መጠሪያ የሚታወቁት ከጂጂጋ የተመረጡ የሶማሌ ክልል ምክር ቤት አባል መሆናቸውን የሚናገሩት አሊ ማሕሙድ አብዲ ‘ያዩትንና የሚያውቁትን በወከላቸው ሕዝብ ስም በግልፅ የሚናገሩ ሰው በመሆናቸው ምክንያት ደኅንነታቸው በተደጋጋሚ አደጋ ላይ መውደቁን’ አመልክተዋል።

‘የክልሉ ችግሮች ናቸው’ ሲሉ አሊ ጌዲ ከዘረዘሯቸው መካከል የፖለቲካና የኢኮኖሚ በደሎች እንደሚፈፀሙ፣ የሰዉ እንቅስቃሴ ገደብ የተጣለበት መሆኑን፣ የሶማሌ ክልል አስተዳደርን የማያስደስት ማንኛውንም ሃሣብ ያወጣ፣ አስተያየት የሰጠ፣ ብርቱና የጭካኔ ቅጣት እንደሚጠብቀው ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ምላሽ የሰጡት የክልሉ ፕሬዚዳንት አማካሪና የዳያስፖራና የሕዝብ ቅሬታ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዲሪሳቅ ኤልሚ (ሳሃኔ) የክልሉ ምክር ቤት አባል አሊ ማሕሙድ አብዲ (አሊ ጌዲ) ክሦች “መሠረተ-ቢስ ናቸው” ሲሉ አስተባብለዋል።

“የሶማሌ ክልል በዘመኑ ሁሉ እንዲህ ዓይነት እጅግ በጣም ጥሩ ጊዜ ላይ ሆኖ አያውቅም፤ ዛሬ ልማት አለን፤ ሰላም አለን፤ በሕዝብ ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መልካም መንግሥት አለን” ብለዋል ሳሃኔ።

ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

Your browser doesn’t support HTML5

ክሥና መልስ በሶማሌ ክልል መንግሥት ላይ