በሻሸመኔ ከተማ ሰዎች እየተገደሉ መኾኑን ተማሪዎች ገለጹ

የሻሸመኔ ከተማ

የሻሸመኔ ከተማ

በሻሸመኔ ከተማ ጨለማን ተገን በማድረግ በሚፈፀሙ ወንጀሎች ሰዎች እየተገደሉ እንደሆነ፤ በሦስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ሰባት ሰዎች መሞታቸውንና ግድያው የሚፈፀመው ደግሞ በፌሮ ብረት እና በስለት እንደሆነ በሻሸመኔ ከተማ የሚኖሩ ተማሪዎች ገለጹ።

ተማሪዎቹ ግድያውን በመቃወም ለተቃውሞ ሰልፍ ቢወጡም ተቃውሞአቸውን ሳያሰሙ ፖሊስ እንደበተናቸው ለአሜሪካ ድምጽ ተናግረዋል። የከተማው ፖሊስ በበኩሉ ሰዎች መገደላቸውን አምኖ የሞቱትም ሁለት ሰዎች ብቻ ናቸው ብሏል።

ካለፉት ሦስት ሳምንታት ጀምሮ በሻሸመኔ ከተማ ውስጥ አሳቻ ቦታን እና ጨለማን ተገን በማድረግ ሰዎች በድንገት እየተገደሉ መኾኑን ተማሪዎች ይናገራሉ። ትብለጥ ጎሳ እና ሞርካ ጌታቸው የተባሉ ተማሪዎች ሀሩን የተባለ የክፍል ጓደኛቸውን ጨምሮ ሰባት ሰዎች በፌሮ ብረት ተመተውና በስለት ተወግተው መገደላቸውን ይገልፃሉ።

የሻሸመኔ ከተማ ፖሊስ ኃላፊ ኮማንደር አለማየሁ ታደሰ ስለ ጉዳዩ ሲጠየቁ ሰዎች መገደላቸውን አምነው የሞቱት ሰዎች ሁለት ብቻ ናቸው ብለዋል። አያይዘውም ሁኔታው ተጋኖ እንደተነገርው አይደለም። ከዚህ በፊትም በተለየ ወንጀል ተከሰው ታስረው የነበሩና የእስር ጊዜያቸውን ጨርሰው የተፈቱ የፈፀሙት ነው። እነሱም ታስረው ፍርድ ቤት ቀርበው ጉዳያቸው ሲታይ ቆይቶ ፍርድቤቱ በሦስቱ ላይ እድሜ ልክ በሁለቱ ላይ ደግሞ 23 ዓመት እስራት ፈርዶባቸዋል ብለዋል።

ያነጋገርናቸው ተማሪዎች እንደሚሉት ጉዳዩ ዘረፋ ቢሆን ኖሮ ግድያው ይፈጸም የነበረው ንብረት ባላቸው ሰዎች ላይ አሊያም ከግድያው በኋላ የተዘረፈ ንብረት ይኖር ነበር ይህ ግን ምንም በሌላችው ተማሪዎች ላይ የተፈጸመ ግድያ ነው ይላሉ።

ዝርዝር ዘገባውን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

Your browser doesn’t support HTML5

በሻሸመኔ ከተማ ሰዎች እየተገደሉ መኾኑን ተማሪዎች ገለጹ