ከሁለት ዓመት ጦርነት በኋላ ኢትዮጵያ ረጅሙን የሠላም ጉዞ ጀምራለች

ፎቶ ፋይል፦ የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ወደ ትግራይ ክልል፣ መቀሌ የህክምና እና የእርዳታ ቁሳቁሶችን ጭኖ ሲጓዝ እአአ 11/2022

ፎቶ ፋይል፦ የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ወደ ትግራይ ክልል፣ መቀሌ የህክምና እና የእርዳታ ቁሳቁሶችን ጭኖ ሲጓዝ እአአ 11/2022

“በዓለም አደገኛ ከሆኑት ግጭቶች አንዱ የነበረውና በሰሜን ኢትዮጵያ ሲካሄድ የነበረው ጦርነት ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት መጀመሪያ ላይ ማቆሚያ ያልነበረው ቢመስልም፣ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ/ም የተኩስ አቁም ሥምምነት በመደረጉ በአገሪቱ ጥንቃቄ የተሞላበት ብሩህ ተስፋ እንዲኖር አድርጓል” ይላል ሮይተርስ ዜና ወኪል በተጠናቀቀው የአውሮፓውያን ዓመት የኢትዮጵያ ሁኔታ ምን ይመስል እንደ ነበር ለማስታወስ ባጠናቀረው ዘገባ።

ለሁለት ዓመት የተደረገው ጦርነት ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ መፍጠሩን። በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን መግደሉን፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩትን ደግሞ የምግብ ተመጽዋች ማድረጉን እንዲሁም በአፍሪካ በሕዝብ ብዛት ሁለተኛ የሆነችውን አገር መረጋጋት አደጋ ላይ ጥሏል።

ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ/ም የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥትና ህወሓት በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ጦርነቱን ለማቆም ተስማምተዋል። ጦርነቱ በሁለቱ ወገኖች መካከል ለረጅም ግዜ ከቆየ መካሰስ በኋላ የተጫረ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በ2010 ዓ/ም ሥልጣን ከመያዛቸው ቀደም ብሉ በነበሩት 30 ዓመታት አገሪቱን ተቆጣጥሮ የነበረው ሕወሃት፣ የጠ/ሚ ዐብይ መንግሥት ክልሎችን ችላ በማለት ሥልጣንን በማዕከል ለመጠቅለል ይፈልጋል ሲል ይከሳል።

ጠ/ሚ ዐብይ በበኩላቸው ህወሓት መልሶ በአገር ደረጃ ስልጣን ለመቆጣጠር ይፈልጋል ሲሉ መልሰው ይከሳሉ። አንዱ የሌላኛውን ትርክት ውድቅ ያደርጋል።

ሕገ-ወጥ ግድያ፣ አስገድዶ መድፈርና ዘረፋን ጨምሮ ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በሁሉም ወገኖች መፈጸማቸውን የተመድ ወኪሎች፣ በኢትዮጵያ መንግሥት የተቋቋመው የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ መገናኛ ብዙሃን (ሮይተርስን ጨምሮ) ሰንደዋል። ሁሉም ወገኖች ክሱን ያስተባብላሉ።

ተኩስ ማቆሙ ዓለም አቀፍ ዕርዳታ በትግራይ አንዳንድ አካባቢዎች እንዲደርስ አስችሏል። ባለፈው ሳምንት ንብረትነቱ የመንግስት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ትግራይ መዲና በረራ ቀጥሏል።

በጦርነቱ ከዐብይ መንግሥት ጎን ሆና የተዋጋችውና፣ የህወሓት ባላንጣ የሆነችው ኤርትራ ባለፈው ሳምንት የተወሰነ ጦሯን ከሁለት ትልቅ ከተሞች ማስወጣቷን ብትጀምርም፣ ጦሯ ትግራይን እስከወዲያኛ ጠቅልሎ ስለመውጣቱ ግን አሁንም ግልፅ አይደለም።

የኤርትራ ጦር ጠቅልሎ እስኪወጣ ህወሓት ትጥቅ ሊፈታ አይችልም፣ ይህ ደግሞ ግጭት እንዲያገረሽ ያደርጋል ሲሉ ዲፕሎማቶችና ተንታኞች ስጋታቸውን ይገልጻሉ::

ጉዳዩ ለምን አንገብጋቢ ሆነ?

በጦርነት በደቀቀችው ሶማሊያ፣ ኬንያና ሱዳን መሃል የምትገኘው ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ የስበት ማዕከል ነች። ከግጭቱ በፊት የመዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶች በአፍሪካ ብዙም ያልተነካ ኢኮኖሚ ወዳላትና ፤ለውጪ ባለሃብቶች በሯን ወደከፈተችው ኢትዮጵያ ጎርፈዋል።

በአፍሪካ ቀንድ ውጤታማ ተደርጎ የሚታየው የኢትዮጵያ ሠራዊት በሶማሊያ በነበረው የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ሃይል ውስጥ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል። ኢትዮጵያ በግሏም ወደ ሶማሊያ ጦሯን ልካለች።

እየቀጠለ ያለና የተበላሸ የሰብዓዊ ሁኔታ አለ። በዩክሬን ያለው ጦርነት በኢትዮጵያ ያለውን አደጋ ትኩረት እንዳያገኝ አድርጎታል ሲሉ የዕርዳታ ወኪሎች ተናግረዋል።

2023 ምን ይመስላል?

ይህ አዲስ የፈርንጆች ዓመት በጥቅምት ወር የተደረሰው ስምምነት ዘላቂ ሰላም ማስፈኑ የሚፈተሽበት ዓመት ነው። ዋና ዋና ችግሮች ግን አሁንም አልተፈቱም።

ከነዚህም ውስጥ ከመንግሥት ጎን ሆነው የተዋጉት የኤርትራና ሌሎችም ሃይሎች መውጣት እንዲሁም በትግራይና በአማራ ክልሎች መካከል በባለቤትነት ይገባኛል ጭቅጭቅ ውስጥ ያሉ መሬቶች ይገኙበታል።

ዓለም አቀፍ አጋሮች ጦርነቱን ለማስቆም ብዙ ሠርተዋል። የአፍሪካ ኅብረት፣ ኬንያና ደቡብ አፍሪካ ለችግሩ አፍሪካዊ መፍትሄ ለመስጠት እጅግ ይሻሉ።

ዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ ተኩስ አቁሙን የማያከብር ማንኛውም ወገን ላይ ማዕቀብ ለመጣል እንድማታቅማማ አስታውቃለች።

የውጪ መዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶችን ፍላጎት ለመቀስቀስ የምትሻው ኢትዮጵያ፣ በመንግሥት ባለቤትነት ተይዞ የቆየውን ኢትዮ-ቴሌኮም 40 በመቶ ድርሻ ለመሸጥ ያላትን ዕቅድ እንደገና እንደቀሰቀሰችና ሙሉ የቴሌፎን አገልግሎት ፈቃድ ለመስጠትም ተዘጋጅታለች።

በቡድን 20 አገሮች በተሰጠው የዕዳ ማስተካከያ ዕድል መሠረት ኢትዮጵያ ያለባትን ዕዳ ማስተካከል ላይ አተኩራለች። ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋምም አዲስ ብድር እንዲሰጣት ትሻለች። ሂደቱ ግን በጦርነቱ ምክንያት ተስተጓጉሏል።