የላሊበላ ከተማ ትላንት በከባድ መሣሪያ ተኩስ ስትናጥ እንዳመሸች ነዋሪዎች ተናገሩ

ቤተ ጊዮርጊስ ላሊበላ

በዐማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን የምትገኘው ታሪካዊቷ የላሊበላ ከተማ፣ ትላንት ረቡዕ፣ በከባድ መሣሪያ ተኩስ ስትናጥ እንዳመሸች፣ ነዋሪዎች ነግረውኛል ሲል፣ የኤኤፍፒ ዜና ወኪል ዘግቧል።

የፌዴራል ኃይሎች፣ የፋኖ ታጣቂዎች ይገኙበታል ብለው ወደገመቱት አካባቢ፣ ከባድ መሣሪያ መተኮሳቸውን ዘገባው አመልክቷል።

በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ ውቅር አብያተ መቅደሶች የሚገኙባት ግንባር ቀደም የቱሪስት መስሕቧ ላሊበላ፣ በፋኖ እና በፌዴራል ኃይሎች መካከል ውጊያ ሲካሔድባት ቆይቷል።

“ከትላንት ረቡዕ ምሽት ጀምሮ፣ የፌዴራል ኃይሎች፣ ከመሀል ከተማዋ፣ ፋኖዎች ይገኙበታል ተብሎ ወደሚገመተው የከተማው ዳርቻ፣ ከባድ መሣሪያ ሲተኩሱ ነበር፤” ሲል፣ ሙሉ ስሙን መስጠት ያልፈለገና አያሌው ተብሎ እንደሚጠራ የገለጸ ነዋሪ ለኤኤፍፒ ተናግሯል።

“ለጊዜው በቤቴ ነኝ፡፡ የፌዴራሉ ጦር በየቤቱ እየዞረ፣ ወጣቶች የፋኖ ደጋፊ ኾነው እንደኹ በመጠየቅ ላይ ነው፤” ሲል አክሏል አያሌው።

አንለይ የተባለ የባጃጅ ሹፌር ደግሞ፣ የተኩሱ ድምፅ ከባድ እንደነበርና ምሽቱን ሙሉ መቀጠሉን፣ እንዲሁም ወታደሮች በውጪ ያገኟቸውን ወጣቶች በሙሉ ይይዙ እንደነበር ተናግሯል፤ ሲል ኤኤፍፒ ዘግቧል።

የ38 ዓመት ዕድሜ እንዳለው የገለጸ ሱቅ ጠባቂ እና ስሙን መግለጽ ያልፈለገ ሌላ ነዋሪ ደግሞ፣ ዛሬ በላሊበላ ከተማ ጸጥታ እንደሰፈነ፣ ባንኮች እንደተከፈቱና አንዳንድ የሕዝብ ማመላለሻዎችም እየሠሩ እንደኾኑ ገልጸዋል፡፡ ኾኖም፣ ለበርካታ ሳምንታት ኢንተርኔት ተቋርጦ እንዳለ ተናግሯል።

“ትልቅ ውጥረት እና ፍራቻ አለ። ወታደሮች ነዋሪዎችን እየደበደቡና እየሰረቋቸውም ነው፤” ሲል አክሏል ነዋሪው።

የፌዴራል ኃይሎች፣ በዐማራ ክልል፣ ከሕግ ውጭ ግድያ እና የጅምላ እስር በመፈጸም ላይ እንደኾኑ፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ባለፈው ዐርብ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የተመድ የሰብአዊ መብቶች ባለሞያዎች ኮሚሽን በበኩሉ፣ በኢትዮጵያ ያለው ኹኔታ “እጅግ አሳሳቢ ነው፤” ሲል፣ ባለፈው ሰኞ ገልጿል። “ሠቆቃ፣ የጦር ወንጀል እና በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች፣ አሁንም በአገሪቱ እየተፈጸሙ ናቸው፤” ብሏል ኮሚሽኑ።