ኢሰመኮ የዐማራ ተወላጆችን እስራት አወገዘ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባለፉት ሳምንታት በዐማራ ክልል የተቀሰቀሰው ከባድ ጦርነት ከፍተኛ ስጋት እንዳሳደረበት ገልፆ፤ በዐማራ ተወላጆች ላይ እየደረሰ ያለውን የእስር ዘመቻ አውግዟል።

ኮሚሽኑን ጠቅሶ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዛሬ ባወጣው ዘገባ፤ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ከመታወጁ በፊትም ሆነ በኋላ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ቅሬታዎች እንደደረሱት ገልጿል። ኮሚሽኑ አክሎም "በአዲስ አበባ ከተማ የዐማራ ተወላጆች የኾኑ ሰላማዊ ዜጎችን እና ከኤርትራ የመጡ ህገወጥ ስደተኞችን በስፋት በመታሰር ላይ ይገኛሉ" ብሏል።

በተመሳሳይ “በክልሉ የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ ባለሥልጣናት በሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆችን በጅምላ አስረዋል” ሲል አሶሽየትድ ፕሬስ የሕግ አዋቂዎችን እና የዓይን እማኞችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

ስማቸውን ለመግለፅ ያልፈለጉ የሕግ ባለሞያዎች፤ አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ዐዲስ አበባ የሚገኙ የዐማራ ተወላጆችን ለእስር መዳረጉን ለዜና ወኪሉ ተናግረዋል። የዐማራ ተወላጆች፤ ከመንገድ ላይ እየታፈሱ፤ በፖሊስ ጣቢያዎች፣ ትምህርት ቤቶች እና ሌሎች ጊዜያዊ ማቆያ ማዕከላት ታስረዋል።

በክልሉ የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ ባለሥልጣናት በሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆችን በጅምላ አስረዋል”

"በመቶዎች" የሚቆጠሩ ሰዎች የታሰሩባቸውን ሰባት ትምህርት ቤቶችን እና ፖሊስ ጣቢያዎችን መጎብኘቱን አንዱ ጠበቃ ሲገልፅ ሌላኛው ደግሞ፤ የፖሊስ ምንጮችን ጠቅሶ በአዲስ አበባ 3,000 ሰዎች መታሰራቸውን ተናግሯል።

ሦስተኛው የሕግ ባለሞያም እንዲሁ፤ ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ ፖሊስ ጣቢያዎች እና ፍርድ ቤቶች ከፋኖ ሚሊሽያ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተያዙ እና የተወነጀሉ በርካታ ወጣቶችን ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በፖሊስ ከተወሰደ ከቀናት በኋላ እንደተለቀቀ የተናገረ አንድ የዐማራ ተወላጅ፤ ባለፈው ሳምንት ሲቪል በለበሱ ፖሊሶች ከመንገድ ላይ የተወሰደው ስለሰሞኑ የዐማራ ክልል ግጭት በስልክ ሲነጋገር ተሰምቶ እንደኾነ ተናግሯል። ወደ ፖሊስ ጣቢያ ከመወሰዱ በፊት በመቶዎች ከሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች ጋራ አንድ ትምሕርት ቤት ውስጥ ታስሮ እንደነበር ተናግሯል።

አንድ ሌላ አስተያየት ሰጪ በበኩሉ፤ አስስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ከመታወጁ በፊት የታሰረው ወንድሙ፤ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ሌሎች እስረኞች ጋራ በአንድ ትምሕርት ቤት እንደሚገኝ ተናግሯል። ወንድሙ የሚገኝበትን እስር ቤት ሁለት ጊዜ የጎበኘው ይሄ እማኝ፤ አብዛኞቹ እስረኞች ወጣት መኾናቸውን ገልጿል።

የፌደራል መንግሥት በበኩሉ ባለፈው አርብ 23 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ሲገልጽ፤ ከታሳሪዎቹም መካከል አንድ የፓርላማ አባል እና ጋዜጠኛ እንደሚገኙበት ታውቋል።

በዐማራ ክልል የታየውን ለወራት የዘለቀ ውጥረት እና የፋኖ ታጣቂዎች በርካታ ከተሞችን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ፤ ከመንግሥት ሓይሎች ጋራ ከባድ ውጊያ ሲካሄድ ቆይቷል።

የጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ መንግሥት ካለፈው ሃምሌ ሃያ ስምንት አንስቶ ለስድስት ወራት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመላው አማራ ክልል ደንግጓል። ይሁን እንጂ ካለፈው ሳምንት መጨረሻ አንስቶ ሁከቱ ቢቀንስም በርካታ ከተሞች አሁንም በሰዐት እላፊ ዐዋጅ ስር ናቸው።

ለሁለት ዓመታት ለዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያው አስከፊ ግጭት ያበቃው ስምምነት ከተደረሰ ሰባት ወራት በኋላ፡ የዐማራ ክልሉ ግጭት በሕዝቧ ብዛት በአፍሪካ ሁለተኛ በሆነችው ሃገር ያለመረጋጋት ስጋት እንዲያገረሽ ምክኒያት ኾኗል።

ኮሚሽኑ በዛሬው መግለጫም፣ በክልሉ የተካሄደው ጦርነት በከባድ መሳሪያ የታገዘ በመኾኑ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ሞት፣ የአካል ጉዳት እና የንብረት ውድመት ማድረሱን አስታውቋል።

የሟቾች ቁጥር በተመለከተ እስከአኹን በመንግሥት ባለሥልጣናት የተገለፀ ነገር የለም። ኤ ኤፍ ፒ በክልሉ በሚገኙ ሁለት ከተሞች ያነጋገራቸውን የሕክምና ባለሞያዎች ጠቅሶ፤ ባለፈው ሳምንት በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን እና የአካል ጉዳት መድረሱን ዘግቧል።

ኢሰመኮ በበኩሉ፤ ካለፈው ነሃሴ 3/ 2015 ዓ.ም ጀምሮ በዐማራ ክልል፤ በዋና ዋና ከተሞች ሲካሄድ የቆየው ከባድ ውጊያ ጋብ ቢልም፡ "በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች መቀጠሉን እና ዘላቂ መፍትሄ እስኪገኝ ድረስም በእጅጉ አሳሳቢ ነው” ብሏል።

መንገዶችን ለመዝጋት የሞከሩ ተቃዋሚዎች መገደላቸውን፤ በአንጻሩ እስር ቤቶች እና ፖሊስ ጣቢያዎች ተሰብረው እስረኞች እንዲያመልጡ መደረጋቸው እና የጦር መሳሪያዎችና ጥይቶች መዘረፋቸውንም ሪፖርቶች መጥቀሳቸውን ዘገባው አመልክቷል።

SEE ALSO: በአንጻራዊ ሰላም ውስጥ በሚገኙት የዐማራ ክልል ከተሞች ነዋሪዎች በከፍተኛ የዋጋ ንረት እያማረሩ ናቸው

በተያያዘ ዜና የዩናይትድ ስቴትስ፣ የአውስትራሊያ፣ የብሪታኒያ፣ የጃፓን እና የኒውዚላንድ መንግሥታት ባለፈው አርብ በጋራ ባወጡት መግለጫ በቅርቡ በዐማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የተከሰቱት ግጭቶች እንዳሳሰቧቸው አስታውቀዋል።

"ሁሉም ወገኖች የሲቪሎችን ደህንነት እንዲያስጠብቁ፣ ሰብአዊ መብቶች እንዲያከብሩ እና ያሉትን ውስብስብ ጉዳዮች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በጋራ እንዲሰሩ እናበረታታለን። በመላው ኢትዮጵያ ዘላቂ መረጋጋት እውን ይሆን ዘንድ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ መስጠቱን ይቀጥላል" ብለዋል፡፡