በዐማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን የነበሩት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአውላላ እና የኩመር የስደተኛ መጠለያዎች መዘጋታቸውን፣ የድርጅቱ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር በምኅጻሩ ዩ.ኤን.ኤች.ሲ.አር ለአሜሪካ ድምፅ አስታወቀ፡፡
Your browser doesn’t support HTML5
ሁለቱም መጠለያዎች የጸጥታ ችግር እንደነበረባቸው፣ የስደተኞች ተቋሙ ሲገልጽ ቆይቷል፡፡
የሱዳንን ጦርነት ሸሽተው እየመጡ ያሉትን ስደተኞች ለማስጠለልም፣ ከኢትዮጵያ የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ጋራ በመተባበር፣ አፍጥጥ የሚባል ዐዲስ መጠለያ፣ በዚያው በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ ውስጥ መከፈቱንም፣ ለአሜሪካ ድምፅ በኢሜይል በላከው መግለጫው አውስቷል፡፡
ዐዲሱ የአፍጥጥ መጠለያ፣ እስከ 12ሺሕ500 ስደተኞችን የመያዝ ዓቅም እንዳለው የገለጸው ዩ.ኤን.ኤች.ሲ.አር፣ በአውላላ እና በኩመር መጠለያዎች የነበሩ ወደ ሦስት ሺሕ የሚደርሱ ስደተኞች ወደዚያው መጓጓዛቸውን ተናግሯል፡፡ በተለያዩ የዐማራ ክልል አካባቢዎች የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ስደተኞችም ወደ ዐዲሱ መጠለያ መግባታቸውንም አስታውቋል።
SEE ALSO: ተመድ በምዕራብ ጎንደር ዞን የሱዳን ፍልሰተኞች ወቅታዊ ሁኔታ እንደሚያሳስበው አስታወቀስለ ጉዳዩ ለአሜሪካ ድምፅ ያብራሩት፣ የኢትዮጵያ የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት የጎንደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሓላፊ አቶ ኢሳይያስ ሎራ፣ በተዘጉት ሁለቱ መጠለያዎች የነበሩት ኹሉም ስደተኞች ወደ ዐዲሱ የአፍጥጥ መጠለያ መግባታቸውን ገልጸው፣ “የተሻለ የጸጥታ ኹኔታ አለው፤ በአቀማመጡም ጭምር ለስደተኞቹ የተመቸ ነው፤” ብለዋል፡፡
ዩ.ኤን.ኤች.ሲ.አርም፣ በአካባቢው ያለው ከባድ ዝናም፣ እንቅስቃሴዎችን እያስተጓጎለ ቢኾንም፣ “ለስደተኞቹ አስፈላጊ አገልግሎቶችን ለማሟላት ጥረት እየተደረገ ነው፤” ብሏል፡፡ ከአካባቢው ኅብረተሰብ እና ባለሥልጣናት ጋራ በመተባበር እየተከናወነ ነው፤ ባለው ሥራም፣ የአፍጥጥ መጠለያ የጸጥታ ኹኔታ የተሻለ እንዲኾን መደረጉን በመግለጫው አመልክቷል፡፡
SEE ALSO: በአውላላ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ጥቃት ሁለት ሱዳናውያን ተገደሉስደተኞቹ በአውላላ እና በኩመር መጠለያዎች ሳሉ፣ የአገልግሎት አለመሟላትና የጸጥታ ችግሮች ሲፈትኗቸው እንደነበር በተከታታይ ዘግበናል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት፣ በትንሹ ሦስት ስደተኞች መገደላቸውንና ብዙዎችም መቁሰላቸውን የሚመለከታቸው አካላት በጊዜው ገልጸዋል፡፡
SEE ALSO: በምዕራብ ጎንደር ኩመር መጠለያ ጣቢያ ዘጠኝ ሱዳናውያን ስደተኞች በኮሌራ ወረርሽኝ እንደሞቱ ተነገረመጠለያዎቹን ለቀው በመውጣት፣ ለሦስት ወራት ያህል መኖሪያቸውን በጎዳና ዳር ያደረጉ ሱዳናውያን ስደተኞች እንደነበሩም ይታወቃል፡፡ ከእነርሱም መካከል 800 የሚደርሱት፣ በያዝነው ነሐሴ ወር መጀመሪያ ላይ ወደ አገራቸው ሱዳን ለመመለስ የእግር ጉዞ መጀመራቸውንም መዘገባችን አይዘነጋም፡፡
ዩ.ኤን.ኤች.ሲ.አርም፣ በስደተኛ መጠለያዎች አካባቢ ይታያሉ ያላቸውና ግድያንና እገታን የመሰሉ ድርጊቶች እያስከተሉ ያሉት የጸጥታ ችግሮች እንደሚያሳስቡት በቀደሙ መግለጫዎቹ አመልክቷል፡፡