በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር፣ የዜጎች ሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ጉዳይ እንዳሳሰባቸው ገልጸው ያሰሙትን የፖሊሲ ንግግር፣ ኢትዮጵያ ትላንት ኀሙስ ባወጣችው መግለጫ ተቃውማለች።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል የወጣው መግለጫው፣ የአምባሳደሩን ንግግር፥ "ሳይጠየቅ" እና "በወጉ ሳይጤን የቀረበ" ሲል ተችቷል።
አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ንግግሩን ያሰሙት፣ ከትላንት በስቲያ ረቡዕ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በታሪካዊ ቅርስነት የተመዘገበንና በቅርቡ እድሳት የተደረገለትን አንድ ሕንጻ በጎበኙበት ወቅት ነው፡፡ የሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች እና ሌሎችም ተጋባዥ እንግዶች ፊት ማሲንጋ ባደረጉት በዚኹ ንግግር፣ “ሕገ ወጥ ግድያ፣ የዘፈቀደ እስራት፣ ጾታዊ እና ሌሎች ጥቃቶችን አስመልክቶ የወጡት ሪፖርቶች” ኹነኛ እልባት ያገኙ ዘንድ ግልጽ እና የተሟላ ፍትሕ ማስገኘት የሚያስችል ሒደት እንዲመቻች ጥሪ አቅርበዋል።
SEE ALSO: በኢትዮጵያ ጊዜያዊ አገር አቀፍ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ዩናይትድ ስቴትስ ጠየቀችአያይዘውም፣ "አገሪቱ ከጦር ሜዳ ይልቅ ከሰላም ብዙ ታተርፋለች፤" ሲሉም፣ “ኢትዮጵያን የማስተዳደር ኃላፊነት ላለበት ለኢትዮጵያ መንግሥት መልዕክት አስተላልፈዋል። "ተቺዎችን ማሰርና ማዋከብ መፍትሔ የሚሹ ችግሮችን አይፈታም፤" ሲሉም አክለዋል።
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ፣ “የተቃውሞ ውንጀላዎችንና ከመንግሥት ሳይጠየቅ የቀረበ ምክርን ያዘለ" ነው ያለውን የአምባሰደሩን ንግግር በመግለጫው አውግዟል።
መግለጫው፣ “የተሳሳተ እና መረጃ የጎደለው፣ በወጉ ያልተመከረበትና ባለማወቅ የተደረሱ ድምዳሜዎችን የያዘ ነው። በኢትዮጵያ እና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል ያለውን ታሪካዊ እና በወዳጅነት የተመላ ግንኙነትንም የሚፃረር ነው፤" በማለትም ነቅፏል።
ማሲንጋ በቀደመው ንግግራቸው፣ ሰላማዊ ዜጎችን “ማፈናቀልን” ጨምሮ በሰው ልጆች ላይ “መከራ ያደርሳሉ” ያሏቸውን “ሁሉንም ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት” ወቅሰዋል።
መንግሥት በአሸባሪነት የፈረጀውን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን ጨምሮ አንጃ ለይተው የሚንቀሳቀሱ - የፋኖ ታጣቂ እና የህወሓት የተለያዩ ቡድኖች ተዋጊዎች፤ ጥያቄዎቻቸውን ከዐመፅ ይልቅ በውይይት እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል።
ዘገባው አያይዞም፣ ከ80 በላይ የልዩ ልዩ ቋንቋ ተናጋሪ ብሔር እና ብሔረሰቦች መኖሪያ እና በአፍሪካ በሕዝቧ ብዛት ሁለተኛ የኾነችው ኢትዮጵያ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በማንነትና ከይዞታ ይገባኛል ጥያቄዎች ጋራ በተዛመደ መጠነ ሰፊ ግጭቶችን ማስተናገዷን አስታውሷል።