"ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ቅደሚ
በኅብረሰባዊነት አብቢ ለምልሚ"
በዘመነ ደርግ የዚህ የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር፣ የግጥሙ ደራሲ አሰፋ ገብረ፡ማርያም ተሰማ ትናንት ዕሑድ ማለዳ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
በብዙዎች ዘንድ እስከነ አያታቸው Assefa GMT /አሰፋ ገብረማርያም ተሰማ/ በመባል የሚጠሩትና እራሳቸውንም በዚያው አጠራር የሚያስተዋውቁት ደራሲና መምህር አሰፋ፣ በተወለዱ በ82 ዓመታቸው ነው፣ ላስ ቬጋስ ከተማ ውስጥ በመኖሪያ በቤታቸው ያረፉት።
ከአባታቸው ከአቶ ገብረማርያምና ከእናታቸው ከወ/ሮ ተዋበች የተወለዱት ደራሲና መምህሩ አሰፋ ጝምጥ፣ ከባለቤታቸው ወ/ሮ አልማዝ በቀለ ጉደታ ጋር ከመሰረቱት ጋብቻ፣ አራት ልጆችን አፍርተዋል።
አቶ አሰፋ ገብረማርያም ተሰማ የሥድስት ልጆች አያትና የአንድ ልጅ ቅም አያትም ነበሩ።
የቬጋስ ነዋሪ መሆናቸውን ለመግለፅ፣ በሚጽፏቸው ማስታወሻዎች መጨረሻ ላይ ሁሉ፣
"አሰፋ ገብረማርያም ተሰማ፣ ከእሳቱ ከተማ" ብለው መፈረም ይቀናቸው እንደነበርም ደብዳቤዎቻቸውን ያነበቡ ሁሉ የሚያውቁት ነው።
ካበረከቱት አስተዋፅዖ በተጨማሪ በአገር ወዳድነታቸው የሚታወቁት የአቶ አሰፋ ገብረማርያም ተሰማ የቀብር ሥነ ሥርዓት፣ በመጭው እሑድ እዚያው ላስ ቬጋስ ውስጥ ቤተሰቦቻቸው፣ ወዳጅ ዘመድና ጓደኞቻቸው በተገኙበት እንደሚፈጸም፣ ከቤተሰብ ያገኘንው መረጃ አመልክቷል።