ኢትዮጵያ ሳተላይት በቅርቡ ሳታመጥቅ አትቀርም

አቶ ተፈራ ዋልዋ

ኢትዮጵያ በመጭዎቹ ከሦስት እስከ አምስት ዓመታት ጠፈር ላይ የራሷ ሳተላይቶች ሊኖሯት እንደሚችሉ የኢትዮጵያ የኢትዮጵያ የኅዋ ሳይንስ ማኅበር የበላይ ጠባቂ አቶ ተፈራ ዋልዋ አስታውቀዋል፡፡

አቶ ተፈራ ዋልዋ ከቪኦኤ ጋር ቃለምልልስ ሲያደርጉ

Your browser doesn’t support HTML5

ኢትዮጵያ ሳተላይት በቅርቡ ሳታመጥቅ አትቀርም

ኢትዮጵያ በመጭዎቹ ከሦስት እስከ አምስት ዓመታት ጠፈር ላይ የራሷ ሳተላይቶች ሊኖሯት እንደሚችሉ የኢትዮጵያ የኢትዮጵያ የኅዋ ሳይንስ ማኅበር የበላይ ጠባቂ አቶ ተፈራ ዋልዋ አስታውቀዋል፡፡

የማኅበሩ መሥራች ሊቀመንበር የነበሩትና አሁን የበላይ ጠባቂው፤ እንዲሁም የእንጦጦ የኅዋ ምርምርና ልዩ ማሠልጠኛ ማዕከል የቦርድ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ተፈራ ዋልዋ ሰሞኑን ለቪኦኤ በተለይ በሰጡት ቃለምልልስ ኢትዮጵያ በአንዳንድ መስኮች በጠፈር ላይ አገልግሎት እራሷን እንድትችል የሚያርግ የራሷ የሰው ኃይልና ተቋም ሊኖራት ይገባል ብለው እንደሚያምኑ ገልፀዋል፡፡

በድኅነት ውስጥ ያለችና የበዙ ችግሮች ያሉባት ኢትዮጵያ ስለጠፈር ማሰቧን በጥርጣሬና በቅሬታ የሚያዩ ወገኖች መኖቸውን አስመልክቶ የተጠየቁት አቶ ተፈራ “የኅዋ ልማት ከድኅነት መውጫ የምጣኔ ኃብት ዘርፍ እንጂ በድኅነት ምክንያት ወደኋላ የሚቀርበት ባለመሆኑ የአስተሳሰብ ድኅነትን አስወግዶ ከተሠራ የታሰበውን ወደ ተግባር መተርጎምና የመስኩ ተጠቃሚ መሆን ይቻላል ብለዋል፡፡

በኅዋ ልማት ኢትዮጵያ አሁን ለተለያዩ አገልግሎቶች የምታወጣውን የኪራይ ክፍያ ለማስቀረትና እንዲያውም አገልግሎቱን ወደመሸጥ ልትገባ እንደምትችልም ሃሣቡ ወደ ተጨባጭ ዝርዝር ዕቅድ መቀየር እንደሚቀረው የጠቆሙት አቶ ተፈራ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ማኅበር ዓርማ

የኢትዮጵያ የስፔስ ሳይንስ ማኀበር በ1996 ዓ.ም በ47 ሰዎች የተቋቋመ የበጎ ፍቃደኞች ማኅበር መሆኑንና አሁን ከእንጦጦ የኅዋ ምርምር ማዕከል ጋር በመሆን ከበርካታ የሃገር ውስጥና የውጭም ምሁራን ጋር እየሠራ ያለ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ስፔስ ሣይንስ ሶሳይቲ የገነባውን የእንጦጦውን ማዕከል ለሃገሪቱ የመንግሥትና የግሉ ዩኒቨርሲቲዎች ባለቤትነት ማስረከቡንና ማኅበሩ በቦርድ አባልነት እንደሚሳተፍ የጠቆሙት አቶ ተፈራ በማዕከሉ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ 18 የፒኤችዲ አጥኝዎች እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡

ሰሞኑን የኢትዮጵያ ስፔስ ሣይንስ ማኅበር የወቅቱ ሊቀመንበር ከሆኑት ከዶ/ር ከላሊ አድሃና ጋር ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሥራ ጉዞ ላይ የሰነበቱት አቶ ተፈራ ዋልዋ ከአሜሪካው የኤሮኖቲክስና የጠፈር አስተዳደር - ናሣ ባለልሥጣናትና ከዋና ዳይሬክተሩ ከቻርለስ ቦልደን ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል፡፡

ውይይቶቻቸው ስላተኮሩባቸው ሦስት ዋና ዋና ነጥቦች አቶ ተፈራ ሲያስረዱ የመስኩን ተማሪዎችና ሠልጣኞች ኢትዮጵያ ሄደው የሚያስተምሩ ሳይንቲስቶች እና የሳተላይት ግንባታን ጨምሮ ሥራውን እየሠሩ የሚያሠለጥኑ መሃንዲሶች ከአሜሪካ የሚገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት አንዱ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

አቶ ተፈራ ዋልዋ

በተጨማሪም የጋራ ምርምር ለማከናወን፣ የአሜሪካዊያኑን በሕዋም ያሉ ያሰቧሰቧቸውንም መረጃዎች ኢትዮጵያዊያኑ ሊያገኟቸው የሚችሉባቸውን ሁኔታዎች መፍጠር፤ እንዲሁም በመካከለኛና በረዥም ጊዜ በትብብር መሥራት የሚቻልባቸው አካባቢዎች ካሉ ስምምነት ላይ መድረስ ይቻል እንደሆነ መነጋገር ከውይይቶቸው መካከል እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

“ከናሳ በኩል ያገኘው አዎንታዊ ምላሽ ጠንካራና ከጠበቅነው በላይ ነው፤ ሊደግፉን ከልባቸው ጥረት እንደሚያደርጉ” ብለዋል አቶ ተፈራ፡፡

“በእንጦጦ የኅዋ ምርምር ማዕከል እነርሱ በምሥራቅ አፍሪካ መሥራት ያልቻሉትን ኢትዮጵያ ልትሠራ እንደምትችልና የጋራ ምርምር ማድረግ እንደሚገባ መንገድ ሲያሳዩን ነበር” ብለዋል አቶ ተፈራ አክለው፡፡

የእርሣቸው ቡድን ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የመጣው የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን የኬንያና የኢትዮጵያን ጉብኝት ተከትሎ በመሆኑ ምናልባት ተልዕኳቸው ከሰፈሩ የፀጥታ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ሳይሆን አይቀርም የሚሉ አንዳንድ ጭምጭምታዎችን አስመልክቶ ኢትዮጵያና አሜሪካ ከሚተባበሩባቸው ሰፊ መስኮች መካከል አንዱ ፀረ-ሽብር እንቅስቃሴ መሆኑ ግልፅ መሆኑን ከመጥቀስ በስተቀር የእርሣቸው ጉዞ ከእንዲህ ዓይነቱ ትብብር ጋር ግንኙነት ይኑረው አይኑረው አላብራሩም፡፡ “ስለዚህ ጉዳይ የሚመለከተውን ቢሮ መጠየቅ የሚሻል ይመስለኛል” በሚል አልፈውታል፡፡

ኢትዮጵያ በመስኩ ከዩናይትድ ስቴትስ ሌላም ከሩሲያ፣ ከደቡብ ኮሪያ፣ ከአውሮፓ ኅብረት፣ ከጃፓን፣ ከቻይና፣ ከሕንድና ከደቡብ አፍሪካ ጋርም እየሠራች መሆኗን የገለፁት አቶ ተፈራ በእንጦጦው የኅዋ ምርምር ማዕከል ውስጥ የፒኤችዲ ተማሪዎችን ከሚያሠለጥኑት መካከል የሩሲያ ፕሮፌሰሮች እንደሚገኙ፣ የደቡብ ኮሪያ የጠፈር ልማት ጀማሪ የነበሩ ሳይንቲስትና መሐንዲስ ኢትዮጵያ ሄደው መሥራታቸውን፣ የአውሮፓ ኅብረት የኅዋ ኤጀንሲ ሰዎች አንዳንዴ ብቅ እያሉ እንደሚያግዟቸው አስረድተዋል፡፡

የእንጦጦ የጠፈር ቅኝት ጣቢያ ግንባታ

ኢትዮጵያ አጠቃላይ ዋጋቸው በዛሬ ምንዛሪ ከስድስት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ ከፍተኛ አቅም ያላቸውን ሁለት ቴሌስኮፖች እንጦጦ የጠፈር ቅኝት ጣቢያ ላይ ተክላለች፡፡

በእንጦጦ የኅዋ ቅኝት ጣቢያ

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ማኅበርና የእንጦጦው የኅዋ ምርምርና ልዩ ሥልጠና ማዕከል የተቋቋሙትና የሚንቀሳቀሱት ከሃገር ውስጥ በሚገኙ ድጋፎች መሆኑን አቶ ተፈራ ጠቁመው የግል ባንኮች፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች፣ የማኅበሩ አባል የሆኑና ያልሆኑም ግለሰቦች በሚሰጧቸው ልገሣዎች መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በተለይ ከማኅበሩ ምሥረታ አንስቶ ለአሥር ዓመታት የቦርድ አባል ሆነው የቆዩት ሼኽ መሐመድ አል አሙዲ ግዙፍ ድጋፍ ማድረጋቸውን አቶ ተፈራ ተናግረዋል፡፡

“ማኅበሩ ከእንግዲህ በልመና መቀጠል አይኖርበትም፤ እንደሃገርና እንደመንግሥት መታሰብ አለበት” ያሉት አቶ ተፈራ በሁለተኛው የሃገሪቱ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ ተገቢውን ቦታ ሊያገኝ እንደሚገባ ያመለክታል” ብለዋል፡፡

አቶ ተፈራ ዋልዋ ከቪኦኤ ጋር ያደረጉትን ሙሉ ቃለምልልስ ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡