የሊዝ አዋጁ ሕገ መንግሥቱን ይጥሣል - መድረክ

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራዊያዊ አንድነት መድረክ በጠራው ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ አዲሱ የሊዝ አዋጅ ህገ መንግሥቱን የጣሰና ዜጎችን ለመቆጣጠር ያለመ ነው አለ።

በስብሰባው ላይ ንግግር ካደረጉት የመድረክ አመራር አባላት አንዱ የአረና ትግራይ ሊቀመንበር አቶ ገብሩ አሥራት ናቸው።

አቶ ገብሩ አዋጁ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ከተመሠረተባቸው መርኆች ውስጥ አራቱን ጥሷል ብለዋል። ከእነዚህም አንደኛው የህዝብ ሉአላዊነትን የሚገልፀው አንቀፅ ስምንት፣ በንዑስ አንቀፅ አንድ “የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው” ይላል፡፡ ቁጥር ሦስት ደግሞ “ሉዓላዊነታቸው የሚገለፀው በዚህ ሕገ መንግሥት መሠረት በሚመርጣቸው የምክር ቤት ተወካዮችና በቀጥታ በሚያደርጉት ተሣትፎ ነው” ይላል።

አቶ ገብሩ በመቀጠል “ይህ የሊዝ አዋጅ ሲወጣ ግን እነዚህ ሁለት ነጥቦች አልተሟሉም” ብለዋል። “የኢትዮጵያ ሕዝብ በቀጥታ አልተሣተፈበትም፤ አዋጁ የህገ መንግሥቱንም የበላይነት የሚፃረር አዋጅ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

አዲሱ የከተማ ቦታን በሊዝ ሥርዓት የማስተዳደር አዋጅ የጣሣቸው ያሏቸውን ሌሎች የሕገ መንግሥቱን መርኆች አብራርተዋል።

አቶ ገብሩና ሌሎች የመድረክ አመራር አባላት ለሕዝብ ንግግር ያሰሙበትን ከመለስካቸው አምኃ ዝርዝር ዘገባ ያድምጡ፡፡