በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በደረሰ የመሬት ናዳ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 229 ደረሰ

በጎፋ ዞን በገዜ ጎፋ ወረዳ በደረሰ ድንገተኛ የመሬት ናዳ ቤተሰቦቻቸውን ያጡ

በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በደረሰ የመሬት ናዳ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 229 ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ።

ይኽ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ፣ በተደረገው ፍለጋ ሴቶችና ሕፃናትን ጨምሮ የ229 ሰዎች አስክሬን መገኘቱን እና ፍለጋውም ተጠናቅሮ መቀጠሉን ቢሮው ጨምሮ ገልጿል።

የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ምስክር ምትኩ ቀደም ሲል ለአሜሪካ ድምጽ በሰጡት አስተያየት፣ የሟቾች ቁጥር 157 መድረሱን ገልፀው የነበረ ሲኾን፣ የክልሉ ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ከደቂቃዎች በፊት በአወጣው መግለጫ፣ ቁጥሩ መጨመሩን እና ከዚህም በላይ ሊጨምር እንደሚችል አስታውቋል።

አምስት ሰዎች ከባድ አካላዊ ጉዳት እንደደረሰባቸው የገለጹት አስተዳዳሪው፣ ዘጠኝ ሰዎች ደግሞ በሕይወት መገኘታቸውንና ለተሻለ ሕክምና ወደ ሳውላ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ተናግረዋል።

ትላንት ሰኞ፣ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም. የጣለውን ከባድ ዝናም ተከትሎ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በተከሠተ ድንገተኛ የመሬት ናዳ፣ ቁጥራቸው የበዛ ሰዎች በአሠቃቂ ኹኔታ መሞታቸውን፣ የገዜ ጎፋ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ምስክር ምትኩ ለአሜሪካ ድምፅ በስልክ አስታውቀዋል።

ዐዲስ የተቋቋመው አስቸኳይ የአደጋ ጊዜ መልሶ ማቋቋሚያ ዐቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሀብታሙ ፌተና፣ አደጋውን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፣ አንድ የፖሊስ አባልንና ሕፃናትን ጨምሮ 96 ወንዶች እና 50 ሴቶች መሞታቸውን ገልጸዋል፤ አምስት ሰዎች ከባድ አካላዊ ጉዳት እንደደረሰባቸውም ተናግረዋል።

የጎፋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ዳግማዊ አየለ በስልክ ለአሜሪካ ድምፅ እንደገለጹት፣ ከትላንት በስቲያ እሑድ ንጋት 12 ሰዓት ገደማ በተከሠተው ናዳ የተዋጡ አምስት ሰዎች ያሉበትን የአንድ ቤተሰብ አባላት ነፍስ ለማዳን በጥረት ላይ የነበሩ 200 በሚኾኑ ነዋሪዎች ላይ ዳግም በደረሰው አደጋ ቁጥራቸው የበዛ ሰዎች ሕይወት አልፏል።

የአሜሪካ ድምፅ ከስፍራው ባገኘው መረጃ፣ በአንድ ጊዜ በመቶዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎቿን ያጣችው ገዜ ጎፋ ወረዳ በከባድ ሐዘን ውስጥ ትገኛለች።

የአሜሪካ ድምፅ ከስፍራው በስልክ ያነጋገረው የገዜ ጎፋ ወረዳ አስተዳደር የሕዝብ ግኑኝነት ኃላፊ አቶ ያለም መሐሪ፣ የወረዳው ማኅበረሰብ በመሪር ሐዘን ውስጥ መውደቁን ጠቅሰው፣ የተገኙትን አስከሬኖች በአንድ ስፍራ የማሰባሰብና ሥርዓተ ቀብራቸውን የመፈጸም ተግባር እየተካሔደ መኾኑን በስልክ አብራርተዋል።

አቶ ያለም፣ የአስከሬን ፍለጋውና የነፍስ አድን ጥረቱ መቀጠሉንና እስከ አሁን ዘጠኝ ሰዎች በሕይወት መገኘታቸውን አስታውቀዋል። ይኸው ጥረት፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ባለሞያዎችንና የሳውላ ማረሚያ ቤት ታራሚዎችን ጨምሮ በጸጥታ ኀይሎች እና በአካባቢው ማኅበረሰብ ትብብር እየተከናወነ መኾኑንም ተናግረዋል።

የናዳ አደጋው የደረሰባት የኬንቾ ሻቻ ግዝዲ ቀበሌ፣ ከዞኑ ዋና ከተማ ሳውላ 15 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ የምትገኝ ሲኾን፣ ጉዳተኞቹም አርሶ አደሮች እና የገጠር ቀበሌ ነዋሪዎች ናቸው።

የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ እንዲሁም የዞኑና የወረዳው አስተዳደሮች ካወጡት የሐዘን መግለጫ ውጭ፣ ከ157 በላይ ዜጎችን ሕይወት ስለቀጠፈው አደጋ በብሔራዊ ደረጃ የተባለ ነገር እስከ አሁን አልተሰማም።