“እንደኬንያ ፕሬዚዳንትና እንደ ኢትዮጵያ ታላቅ ወዳጅ፤ እንደምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ ሊቀመንበር፤ እንደ አፍሪካ፣ ፓሲፊክና ካሪቢያን ሃገሮች ድርጅት ተቀማጭ ፕሬዚዳንት፤ እንደበይነመንግሥታዊው የልማት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ንቁ አባል፤ እንደአፍሪካ ኅብረት የሰላምና ደኅንነት ምክር ቤት አባል፤ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት እንደ አፍሪካ ተጠሪ፤ ይህ ውጊያ ከተጫረ አንስቶ አስጨናቂው ቀውስ ፍፃሜ እንዲኖረው በንቃትና በትጋት ስጥር ቆይቻለሁ” ብለዋል ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ
ኬንያታ “ጥሪ ለኢትዮጵያ መንግሥትና ህዝብ” በሚል ርዕስ ትናንት ያወጡትን ደብዳቤ የጀመሩት የኢትዮጵያን ምንነትና ትርጉም አጉልተው በማሳየት ነበር።
“ኢትዮጵያ አፍሪካ ውስጥና በዓለም ዙሪያ በተበተነው አፍሪካዊም እይታ ትንግርት ሃገር ነች” ብለዋል።“የድንቅ ኅብረብዝኃነት፤ በሺሆች ዓመታት የሚመዘዝ ቀልብ ነጣቂ ታሪክ ሃገር”
“እንደኔዪቱ ሃገር ኬንያ - ሲሉ ቀጠሉ ፕሬዚዳንት ኬንያታ - ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛና ማለምለሚያ በመሆኗ ገንና ትታወቃለች።”
“የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሥራች ሃገር የሆነችው ኢትዮጵያ ብዙ ሃገሮችና ህዝቦች ስለአርነታቸው እንዲቆሙ፣ ቅኝ አገዛዝን፣ ኢምፔሪያሊዝምንና ሌሎችም የብዝበዛ ዓይነቶችን በመጋፈጥ ነፃነትን እንዲጠብቁ አነቃቂ ፋና ሆናቸዋለች” ብለዋል።
ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የጦርነቱን አጀማመርና ሁኔታ ባስታወሱበትና ለአዲስ አስተሳሰብና መንገድ ምክር በለገሱበት ሃሳባቸው “ህግና ሥርዓትን እንዲሁም በሃገሪቱ ውስጥ ፀጥታና ደኅንነትን ለመጠበቅና ለማበረታታት በቆመው የመንግሥት መዋቅር ላይ በተሠነዘረው እጅግ አሳዛኝና አዋራጅ በሆነ ጥቃት ምክንያት የተነሳው አሳዛኝ የውስጥ ቀውስ ከተጀመረ አንድ ዓመት ሞላው” ብለዋል።
“የቀውሱ መነሻዎች ምንም እንኳ እንደሚስተዋለው መራርና ተቀባይነት የሌላቸው ቢሆኑም እየቀጠለ ላለው መከራና ግድያዎች እንዲሁም አሁን ሃገሪቱን እያዳረሰ ላለው ግልፅ ጦርነት መቀጠል እንደማሳመኛ ምክንያትነት ሊቀጥሉ አይገባም” ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።
ምንም እንኳ “በቀውሱ ዙሪያ ገሃድ የሆኑ ሁኔታዎች ቢኖሩም” ያሉት ኬንያታ ጦርነቱ መቆም እንዳለበት ግፊት ለማሳደር የቢሯቸውን ሙሉ ኃይል መጠቀማቸውን ተናግረዋል።
ለቀውሱ ፍፃሜ ለማበጀት ከአፍሪካና ዩናይትድ ስቴትስን፣ ዩናይትድ ኪንግደምን፣ ፈረንሳይን፣ የአውሮፓ ኅብረትን ጨምሮ ከሌሎችም የዓለም ታላላቅና ኃያላን ሃገሮች መሪዎች ጋር መመካከራቸውን፣ ከመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሃፊና ከአፍሪካ ኅብረት ሊቃነመናብርት ጋር መወያየታቸውንም አመልክተዋል።
ከአንድ ዓመት በኋላ ግጭቱ ከመቆም ይልቅ እየተባባሰ መምጣቱ በጥልቅ እንዳሳሰባቸው ኬንያታ ጠቁመው ውጊያው በቀጠለ መጠን የሞቱ ብዛትም እየጨመረ መምጣቱን፣ የመፈናቀሉ ሁኔታም መበርታቱንና የሃገሪቱ ሰብዓዊ ሁኔታ እየተበላሸ መሆኑን ገልፀዋል።
“ይህ ሁሉ እየሆነ ያለው ደግሞ በመዘዞችና በማስተጓጎል ገፅታዎቹ በታጀበውና ይበልጡን ፈተናውን እጅግ ተጎጂ የሆኑት በሚሸከሙበት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ውስጥ መሆኑ አብዝቶ ያሳዝናል” ብለዋል።
በዋነኞቹ ተዋንያን መካከል ትርጉም ያለው ንግግር ያለመደረጉ አብዝቶ የሚያሳስባቸው መሆኑን የጠቆሙት ኬንያታ “የኢትዮጵያ ቅን ወንድና ሴት ልጆች ተሰብስባችሁ በዚህ የከበደ ጊዜ የሰላም መፍትኄ እንድትፈልጉ ጥሪዬን አቀርባለሁ” ብለዋል።
“በውዱ የአመራር ወንድሜ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመሩ የኢትዮጵያ መንግሥት ወንዶችና ሴቶች፣ እንዲሁም ከመንግሥቱ ጋር ውጊያ የገጠሙትን የሚመሩ ወንዶችና ሴቶች፤ መዋጋት አሁኑኑ አቁመው ለንግግር ለመቀመጥ የሚያስችላቸውን ምክንያት ማግኘት ይኖርባቸዋል” ብለዋል ኬንያታ፤ “ይህንን ማንም ሊያደርግላቸው፤ ቀውሱን ለማቆም የፖለቲካ ወኔ ከሌላቸው ምንም ዓይነት ጣልቃገብነትና ጉትጎታ ሊያቆምላቸው አይችልም” ሲሉ አክለዋል።
“በአደባባይና በግላጭ አብረው ሆነው መሣሪያ እንዲያስቀምጡና መዋጋት እንዲያቆሙ፤ እንዲነጋገሩና ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የሚያደርግ መንገድ እንዲያገኙ ጥሪዬን አቀርብላቸዋለሁ” ብለዋል።
“ኬንያ፣ አፍሪካ፣ ዓለም ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም ወርዶ ማየት ይፈልጋሉ - አሉ ኬንያታ በደብዳቤአቸው ማጠቃለያ - የሰላም ጉዞ ለመጀመር ቀኑ ዛሬ መሆን አለበት፤ ኢትዮጵያዊያን እራሳቸው ይበጀናል በሚሉት ሂደት ለማገዝ ዝግጁ ነን።”
ለዚህ የፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ደብዳቤ ትዊተር ላይ ምላሽ የሰጡት የዩናይትድ ስቴትስ የዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር “የማንቂያ ጥሪ” ብለውታል።
“የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው ሁኔታ የማንቂያ ጥሪ እያሰሙ ናቸው፤ ውጥረት ማርገብና መደራደር እንደሚያስፈልግ እየተጣሩ ነው” ብለዋል ፓወር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የምሥራቅ አፍሪካ ሃገሮች የጋራ ልማት ባለሥልጣን (ኢጋድ) አባል ሃገሮች መሪዎች በኢትዮጵያ ቀውስ ጉዳይ ላይ እንዲመክሩ ለፊታችን ኅዳር 7/2014 ዓ.ም. ስብሰባ መጥራታቸውን የዩጋንዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ኦኬሎ ኦሪየምን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል።
የዩጋንዳው ፕሬዚዳንት ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር እየተነጋገሩ መሆናቸውን ሚኒስትሩ ገልፀው “የትግራዩ ቡድን ለድርድርና ተኩስ ለማቆም ዝግጁ አለመሆኑ ፕሬዚዳንቱን አሳስቧቸዋል” ማለታቸውን የዜና አውታሩ ፅፏል።
በሌላ በኩል ግን ኢጋድ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ተዋጊዎቹ የኢትዮጵያ ወገኖች ከግጭት እንዲታቀቡ፣ በፀብ መፈላለጋቸውን በአስቸኳይ እንዲያቆሙና ተኩስ ማቆም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እንዲመክሩ መጠየቁንም ሮይተርስ ዘግቧል።
ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ፡፡
Your browser doesn’t support HTML5