በልዩ ልዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች፣ ለፋሲካ በዓል የሚኾኑ ግብይቶች ከወትሮው ደምቀው በመካሔድ ላይ ናቸው፡፡
በመጪው የፋሲካ በዓል ዋዜማ፣ አንዳንድ የፍጆታ ምርቶች ቅናሽ ሲያሳዩ፣ ጭማሬ ያሳዩ መኖራቸውንም አስተያየት ሰጪዎች ገልጸዋል፡፡
የተለያዩ ምርቶች ግብይት ባደመቁት በአዲስ አበባ ሾላ ገበያ፣ አግኝተን ካነጋገርናቸው አስተያየት ሰጪዎች፣ ጉልላት ዳኛቸው አንዱ ነው፡፡
ተዘዋውረው በቃኟቸው የበዓል ፍጆታ ምርቶች ላይ፣ ከወትሮው የተወሰነ የዋጋ ጭማሬ እንዳለ የሚገልጹት አቶ ትልቁዓለም ተስፋዬ ደግሞ፣ መንግሥት የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋትና ለኑሮ ውድነቱ ምክንያት ነው ያሉትን ሰላምን ለማረጋገጥ መሥራት እንዳለበት ይመክራሉ፡፡
በሌላ በኩል፣ ከአምራቹ ቀጥታ ለማኅበረሰቡ ምርት እንዲደርስ በሚል በተለያዩ አካባቢዎች የተቋቋሙ አነስተኛ የግብይት ስፍራዎች እና የሸማች ማዕከላት ተቋቁመዋል፡፡ ማዕከላቱ፣ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡ መኾናቸው፣ የዋጋ ንረት ጫናውን እየቀነሰ እንደሚገኝ፣ በሸመታ ላይ ያናገርናቸው ሸዋዬ ደቻሳ እና ወርቅነሽ ዘገዬ ያስረዳሉ፡፡
በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎችም፣ የበዓል ግብይቶች በመከናወን ላይ ናቸው፡፡ ግጭት ከቀጠለበት የአማራ ክልል መዲና ባሕር ዳር ከተማ በስልክ ያናገርናቸው አንድ አስተያየት ሰጭ፣ ስለ በዓሉ ድባብ እና ስለገበያው ኹኔታ አስረድተዋል፡፡
ሌላው በአንዳንድ ስፍራዎቹ ግጭት ካለበት የኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ዞን ነዋሪ የኾኑት አስተያየት ሰጭ ደግሞ፣ እርሳቸው ባሉበት አካባቢ ያለው ድባብ የተቀዛቀዘ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡
ከመቐለ እና ሐዋሳ ከተሞች አስተያየታቸውን የሰጡን ነዋሪዎችም፣ በየከተሞቹ የበዓል ግብይቱ ደምቆ እየተካሔደ እንደሚገኝ ገልጸው፣ የዋጋ ጭማሬ እና መጠነኛ ቅናሽ ያለባቸው ምርቶች ስለመኖራቸው አክለው አመልክተዋል፡፡