ዶ/ር ስለሺ በቀለ ከአሜሪካ ድምፅ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ጉዳዩ የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የግብፅ ብቻ መሆኑን አመልክተው “ጉዳዩን በጥልቀት ሳያውቁ የኢትዮጵያን መብት ነጥቆ ‘በዚህ ጊዜ ሙሉ፤ በዚህ ጊዜ አትሙሉ’ ማለት ተገቢ አይመስለንም” ብለዋል።
በሦስቱ ሃገሮች መካከል ስምምነት ተፈረመም አልተፈረመ ኢትዮጵያ ግድቡን ከፊታችን ነኀሴ ጀምሮ መሙላት እንደምትጀምር፣ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ኃይል አመንጭ መዘውሮች (ተርባይኖች) የዛሬ ዓመት መጋቢት ውስጥ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምሩ ተናግረዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ እያነጋገረቻቸው ያለችው በእኩልነት መንፈስ ሳይሆን ተጋፊ በሆነ፣ በአመሳሶ ስሜትና ሉዓላዊነትን ሊዳፈር የሚችል ውጤት በሚያስከትል አካሄድ እንደሆነም የተናገሩት የኢትዮጵያ የውኃ፣ የመስኖና የኢነርጂ ሚኒስትር መንግሥታቸው “ሁኔታዎችን ለዓለምአቀፍ ማኅበረሰብ ለማሳወቅ በተለያዩ መንገዶች እያደረገ ነው” ያሏቸውን ጥረቶች አብራርተዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ የገንዘብ ሚኒስቴር ሃገሮቹ እንዲፈርሙበት ያዘጋጀውና ግብፅ ፈርማበታለች የተባለው ሠነድ “ኢትዮጵያ በውኃው ላይ ያላትን መብት ሙሉ በሙሉ የሚገፍፍ፣ የማታውቃቸውን የቅኝ ግዛት ዘመን ውሎችን ያለፍላጎትና ተሣትፎዋ ያስገባ፣ በድርቅና በከበዱ የተፈጥሮ ሁኔታዎች ጊዜያት ውኃውን ከግድቧ አሟጥጣ እንድታጠነፍፍ የሚያስገድድ እንደሆነ፣ እንዲሁም ሌሎችም መብቶቿን የሚዳፈሩና የሚገፍፉ አንቀፆች የሰፈሩበት” እንደሆን ሚኒስትሩ ገልፀዋል።
አንዳንድ የግብፅ ባለሥልጣናትና ፖለቲከኞች ስለሚያሰሟቸው ዛቻዎችም ተጠይቀው “ወደ ግጭት የሚወስድ ምንም ምክንያት በሌለበት ሁኔታ ትርጉም የለሽ ነው” ሲሉ አጣጥለዋቸዋል። “አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም ኢትዮጵያም ያሉ አቅምና ኃይሎቿን አሰባስባ እራሷን ለመከላከል አትተኛም” ብለዋል።
“የናይልን ውኃ ሰማንያ ስድስት ከመቶ የምታመነጭና የምታዋጣ ሃገር በተፈጥሮ መብቷ እንዳትጠቀም ሊያደርጋት የሚችል ምንም የለም” ያሉት የኢትዮጵያ የውኃ፣ የመስኖና የኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ስለሺ በቀለ “ሁሉንም ተጠቃሚ ከሚያደርግ በስተቀር በማንም ላይ ጉዳት በማያደርሰው የኅዳሴ ግድብ ውኃ አሞላልና ሥራ አመራር ላይ ውይይቱና ድርድሩ ይቀጥላል” የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ የውኃ፣ የመስኖና የኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ስለሺ በቀለ ከቪኦኤ ጋር ያደረጉትን አዲስ ቃለ-ምልልስ ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።
Your browser doesn’t support HTML5