አብዲ ኢሌ "ለማምለጥ አልሞከርኩም" አሉ - ፖሊስ የማምለጥ ሙከራ ክስ አሰምቶባቸዋል

አብዲ ኢሌ

ከተያዙበት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ማረፊያ ክፍል የማምለጥ ሙከራ አላደረግኩም ሲሉ የሶማሌ ክልል የቀድሞ ፕሬዚዳንት አብዲ መሐመድ (አብዲ ኢሌ) ዛሬ ለችሎት ተናግረዋል። ባለፈው ሐምሌ መጨረሻ ሶማሌ ክልል ዋና ከተማ ጂግጂጋ ውስጥ ተነስቶ ከነበረው ሁከትና ብጥብጥ ጋር በተያያዘ ተይዘው እሥር ላይ የሚገኙት አቶ አብዲ መሐመድ (አብዲ ኢሌ) ያረፉበትን በር መስተዋት ሰብረው ለማምለጥ ሞክረዋል ሲል ፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አስታውቋል።

ከተያዙበት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ማረፊያ ክፍል የማምለጥ ሙከራ አላደረግኩም ሲሉ የሶማሌ ክልል የቀድሞ ፕሬዚዳንት አብዲ መሐመድ (አብዲ ኢሌ) ዛሬ ለችሎት ተናግረዋል።

ባለፈው ሐምሌ መጨረሻ ሶማሌ ክልል ዋና ከተማ ጂግጂጋ ውስጥ ተነስቶ ከነበረው ሁከትና ብጥብጥ ጋር በተያያዘ ተይዘው እሥር ላይ የሚገኙት አቶ አብዲ መሐመድ (አብዲ ኢሌ) ያረፉበትን በር መስተዋት ሰብረው ለማምለጥ ሞክረዋል ሲል ፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አስታውቋል።

አብዲ ኢሌ ካለፈው ሣምንት አንስቶ ያሳዩት የነበረው ጠባይ የማምለጥ ሙከራ የማድረግን ሃሣብ ይጠቁም እንደነበረ ለቪኦኤ የጠቆሙት የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የተደራጁ ድንበር ተሸጋሪና ሃገራዊ ጉዳት የሚያስከትሉ ወንጀሎች ጉዳይ ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ፀጋ “ከጠባቂዎች ጋር ግብ ግብ ይፈጥሩ ነበር” ብለዋል።

አቶ አብዲ መሃመድ እንዲያርፉ የተደረገበትን አዲስ አበባ ፖሊስ ኮማሽን ውስጥ የሚገኝ ክፍል በር መስተዋት መስበራቸው ሊያመልጡ ሞክረዋል የሚል እምነት ማሳደሩን ዳይሬክተሩ አቶ ፍቃዱ ፀጋ ከቪኦኤ ዘጋቢ ሶራ ሃለኬ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አመልክተዋል።

በሌላ በኩል ግን የፌደራሉን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀጠሮ ውሎ የጠቀሰ አንድ የፋና ብሮድካስቲንግ ዘገባ “ድርጊቱን አልፈፀምኩም” ያሉት ተከሣሹ አቶ አብዲ መሐመድ ስማቸውን ለማጥፋትና ድብደባ ለመፈፀም ሆን ተብሎ የተደረገ ሴራ እንደሆነ ተናግረዋል።

ምቹ ባልሆነ እስር ቤት መታሰራቸውን፣ የአዕምሮ ህመምተኛ የሆነ ታሳሪ የታሰሩበትን ክፍል በር ገንጥሎ በመግባት ሁለት ቀን ጉዳት ሊያደርስባቸው እንደሞከረና ይህም በደህንነታቸው ላይ ስጋት እንደፈጠረባቸውም መግለፃቸውን የፋና ዘገባ ጠቁሟል።

በአብዲ መሐመድ የክስ መዝገብ ተጨማሪ መረጃ ለማሰባሰብ የአሥር ቀን የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ፖሊስ በጠየቀው መሠረት ፍርድ ቤቱም ምርመራውን እያካሄደ ያለው ፖሊስ ውጤቱን ጥቅምት 19 / 2011 ዓ.ም ይዞ እንዲቀርብ በማሳሰብ ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን ዘገባው አመልክቷል።