የኢትዮጵያ "በጀት እንዳይፀድቅ" ጥያቄ ውድቅ ተደረገ

  • ቪኦኤ ዜና

ፎቶ ፋይል፦ አዲስ አበባ ከተማ

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ግጭት የተፈፀሙ የመብት ጥሰቶችን እንዲያጣራ ለተቋቋመው መርማሪ ቡድን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በጀት እንዳይፈቅድ ኢትዮጵያ ያቀረበችውን ጥያቄ በመንግሥታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ውድቅ ተደርጓል።

193 አባላት ያሉት የመንግሥታት ድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ፣ የበጀት ኮሚቴ ትናንት ባደረገው ስብሰባ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ በሚካሄደው ጦርነት የተፈፀሙ የመብት ጥሰቶችን አጣርቶ ክስ መመስረት የሚያስችል ምርመራ እንዲያካሂድ ላቋቋመው ቡድን በጀት እንዲሰጠው ወስኖ አፅድቋል።

በትናንቱ ስብሰባ ኢትዮጵያ በጀቱ እንዳይፈቀድ ላቀረበችው ጥያቄ ድጋፍ የሰጡ ሀገራት 27 ሲሆኑ 66 የተቃውሞ፣ 39 ሀገራት ደግሞ ድምፀ ታእቅቦ አድርገዋል። ኢትዮጵያ - ውሳኔው በምዕራብ ሀገራት ለፖለቲካ ዓላማ የተገፋ ነው - በማለት እንደማትተባበር ያስታወቀች ሲሆን - ከድምፅ አሰጣጡ በፊት ለበጀት ኮሚቴው ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ዲፕሎማት ወይዘሮ ለምለም ፍሰሀ "ኢትዮጵያ ይህንን አይነት አሰራር እንደማትቀበልና ቡድኖ ወደ ኢትዮጵያ መግባት እንደማይፈቀድለት" አስታውቀዋል።

ወይዘሮ ለምለም አክለው "ይህ ቡድን የሰብዓዊ መብትን የማራመድ ዓላማ ያለው አይደለም። ይህ የፖለቲካ ሂደት መሆኑ ግልፅ ነው" ሲሉ ተናግረዋል። የበጀት ኮሚቴው የፈቀደው በጀት ብዙ ማስተካከያ የተደረገበት እና የተባበሩት መንግሥታት ከጠየቀው ያነሰ መሆኑን ዲፕሎማቶች ለሮይተርስ ተናግረዋል።

በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት በተባበሩት መንግሥታት አመራር እና ማሻሻያ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ክሪስ ሉ፣ "ዩናይትድ ስቴትስ እንድ አንድ የመንግሥታት ድርጅቱ አካል፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽኑ ያሳለፈውን ውሳኔ ማክበር እና ወደ ተግባራዊ እንዲሆን የማድረግን አስፈላጊነት ታረጋግጣለች" ብለዋል።

ለበጀት ኮሚቴው ንግግር ያደረጉት ክሪስ ሉ፣ "እንደዚህ አይነት ኃላፊነቶች በበጀት ውሳኔ ምክንያት እንከን ሊገጥማቸው አይገባም" ሲሉ ጨምረው አስረድተዋል። በህዳር ወር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ በኢትዮጵያ መንግሥት ከተቋቋመው የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር በመሆን በጋራ ባካሄዱት ምርመራ በጦርነቱ በተሳተፉ ሁሉም አካላት የጦር ወንጀል መባል የሚችል የመብት ጥሰት መፈፀሙን አስታውቀው ነበር።

የመንግሥታት ድርጅቱን ወሳኔ ተከትሎ አስተያየት የሰጡት በመንግሥታት ድርጅቱ የሂዩማን ራይትስ ዎች ዳይሬተር የሆኑት ሉዊስ ቻርቦኑ "የመንግሥታት ድርጅቱ አባል ሀገራት፣ ኢትዮጵያ ለሰብዓዊ መብቶች መርማሪ ቡድን በጀት በማስከልከል ከጦር ወንጀሎች እና ሌሎች የመብት ጥሰቶች ተጠያቂነት ለማምለጥ ላደረገችው ጥረት ዛሬ ጠንካራ መልዕክት አስተላልፈዋል።" ብለዋል።

የመንግስታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሬክ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ፣ አጣሪ ኮሚቴው በጀት ሊፈቀድለት እንደሚገባ ተናግረው፣ በኢትዮጵያም ይሁን በሌላ የትኛውም አለም የሚፈፀም የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምርመራ ሊደረግበት ይገባል ማለታቸውን ሮይተርስ ጠቅሷል።