ዘ ኢኮኖሚስት የኢትዮጵያ መንግሥት ጋዜጠኛውን ከአገር ማስወጣቱን አስታወቀ

ፎቶ ፋይል - የዘ ኢኮኖሚስት መጽሄት ቅጂ በማዕከላዊ ለንደን፣ ብሪታንያ እአአ ነሃሴ 12/2015

- የሀረሪ ክልል መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ ጋዜጠኛ መታሰሩ ተገለጸ

ዘ ኢኮኖሚስት መጽሄት የኢትዮጵያ መንግሥት በተሳሳተ የጋዜጠኝነት አሰራር የወነጀለውን ጋዜጠኛውን ታም ጋርድነርን ከአገር ማስወጣቱን አስታወቀ።

ዘ ኢኮኖሚስት ትናንት ሰኞ ባወጣው መግለጫ ጋዜጠኛው፣

"ሥራውን ሙያውን ባከበረ፣ አድላዊ ባልሆነ ብዙ ጊዜም ያለፍርሃት በድፍረት የሚያከናውን ጋዜጠኛ ነው" ሲል ተከላክሎ በኢትዮጵያ መንግሥት መባረሩን አረጋግጧል።

የኢትዮጵያ መንግሥት "አዲስ አባበ ተመድቦ ይሰራ የነበረውን ጋዜጠኛችንን ታም ጋርድነርን ባለፈው አርብ እአአ ግንቦት 13 ቀን የሥራ ፈቃዱን ነጥቆ በአርባ ስምንት ሰዓት ውስጥ ከሀገሪቱ እንዲወጣ አዞታል" ብሏል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ለኢኮኖሚስቱ ጋዜጠኛ ታም ጋርድነር በጻፈው እና በትዊተር ገጹ ባወጣው ደብዳቤው የሥራ ፈቃዱ መነጠቁን እና ኢኮኖሚስት በምትኩ ሌላ ጋዜጠኛ መላክ እንደሚችል ማሳወቁ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፈው የአውሮፓ 2021 ግንቦት ወር ውስጥ የኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ዘጋቢ የነበረውን ሳይመን ማርክስ ማስወጣቱን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ አያይዞ አስታውሷል።

ጋዜጠኛው ታም ጋርድነር ጦርነት ሲካሄድበት ወደቆየው የትግራይ ክልል ተጉዞ እንደነበር የገለጸው ዘ ኢኮኖሚስት "ትግራይን ጨምሮ ባጠቃላይ ከኢትዮጵያ ያጠናቀራቸው ዘገባዎቹ የሙያ መስፈርቱን ያሟሉ ከአድልዎ ነጻ የሆኑ አዘውትሮም በድፍረት ያጠናቀራቸው ዘገባዎች ናቸው" ብሏል።

በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ የኢኮኖሚስት ጋዜጠኛው የሥራ ፈቃዱን ተነጥቆ መባረሩ እንዳሳዘነው ገልጾ ጋዜጠኞች ሙያዊ ሥነ ምግባር በጠበቀ መንገድ ህዝቡን ወክለው መስራት መቻል አለባቸው" ብሏል።

በኢትዮጵያ የሚሰሩ ጋዜጠኞች በቀል ወይም ከህግ ውጭ መታሰር ይደርስብናል ነጻነታችንን ወይም ህይወታችንን እናጣለን ብለው ሳይፈሩ የመስራት መብታቸው እንዲከበር ሙሉ በሙሉ እንደግፋለን ሲል የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ አስታውቋል።

የሀረሪ ክልል የመገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ ጋዜጠኛ እና የመዝናኛ ፕሮግራም አዘጋጅ ሙሄዲን አብዱላሂ

በሌላ ዜና የሀረሪ ክልል መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ ጋዜጠኛ እና የመዝናኛ ፕሮግራም አዘጋጅ ሙሄዲን አብዱላሂ ከስምንት ቀን በፊት ከሥራ ቦታው ተወስዶ መታሰሩ ተገለጸ።

የቪኦኤ የአፋን ኦሮሞ ክፍል በወሊድ ፈቃድ ላይ የምትገኘውን ባለቤቱን ጋዜጠኛ ሄለን ጀማልን አነጋግሯል።

የሀረሪ ክልል ምክትል ኮሚሽነር ኡመር ኡሜ ለቪኦኤ በሰጡት ቃል ሙሄዲን

"ሁከት ሊያስነሳ የሚችል መልዕክት በማኅበራዊ መገናኛ በማጋራቱ ጉዳዩ እየተመረመረ ነው" ብለው ዛሬ ፍርድ ቤት የዋስ መብት ሰጥቶታል" ብለዋል።