ኢትዮጵያ የተመድ ሰባት ባለሥልጣናት እንዲወጡ አዘዘች

  • ቪኦኤ ዜና

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰባት ባለሥልጣናት በ72 ሰዓታት ውስጥ ከሃገር እንዲወጡ መወሰኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ አስታወቀ።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ዛሬ ባወጣው መግለጫ የተባበሩት መንግሥታት የህፃናት መርጃ ድርጅት /ዩኒሴፍ/ እና የጅርጅቱ የሰብዓዊ ጉዳዮች የኢትዮጵያ ቢሮዎች ኃላፊዎችንና አንድ የሰብዓዊ መብቶች ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ አንድ የቡድን ኃላፊን ጨምሮ ሰባቱ የድርጅቱ ሠራተኞች በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ ገብተዋል በሚል መንግሥት “ተቀባይነት የሌላቸው ግለሰቦች” ወይም የ“ፔርሶና ኖን ግራታ” ውሳኔ ያወጣባቸው መሆኑን አመልክቷል።

መሥሪያ ቤቱ “ፔርሶና ኖን ግራታ” የተላለፈባቸውን ሠራተኞች ስሞች ዝርዝር ያወጣ ሲሆን በሰባ ሁለት ሰዓታት ውስጥ ከሃገር እንዲወጡ መወሰኑንም አስታውቋል።

ይህ ዜና እስከተቀረፀበትና ለሥርጭት እስከገባበት ሰዓት ከመንግሥታቱ ድርጅትም ሆነ ከተቋማቱ ወይም ከግለሰቦቹ በይፋ የወጣ አስተያየት ወይም መልዕክት የለም።