ተፈናቃዮች በከፍተኛ ችግር ላይ መሆናቸውን ገለጹ

ባሌ

ከኢትዮጵያ ሶማሌና ከሶማሌላንድ የተለያዩ ከተሞች የተባረሩ ተፈናቃይ የኦሮሞ ተወላጆች፤ በባሌ ዞን ውስጥ የምግብ እጥረትን ጨምሮ ለተለያዩ ችግሮች መጋለጣቸውን ገለጹ። የዞኑ አስተዳዳሪ ፤ “እርዳታ እየሰጠንና የተቻለንን እያደረግን ነው ለሁሉም ግን በቂ ነው ማለት አንችልም።” ብለዋል።

Your browser doesn’t support HTML5

ተፈናቃዮች በከፍተኛ ችግር ላይ መሆናቸውን ገለጹ

በሶማሌና በኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ላለፉት ሰባት ወራት በከፍተኛ ሁኔታ ተባብሶ የቆየው ግጭት ያስከተለው መፈናቅል ቁጥራቸው የበዛ ኢትዮጵያውያንን ለችግር ዳርጓል።

የባሌ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አብዱልቃድር ሁሴን በዞኑ ስምንት ወረዳዎች ውስጥ ከ100 ሺሕ የሚበልጡ ከሶማሌ ክልልና ከሶማሌ ላንድ የተባረሩ ዜጎች እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ተፈናቃዮቹ በበኩላቸው ይኖሩበት ከነበረ ቀዬ ንብረታቸውን ጥለው ከተሰደዱ በኋላ ለወራት በችግር ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ።

የምግብ እጥረት ዋነኛ ችግራቸው መሆኑን የሚናገሩት ተፈናቃዮቹ መጠለያ፣ አልባሳትና መቋቋሚያ ሥራ እንደሌላቸው ገልፀውልናል።

በሥራ ላይ የነበሩ ወጣቶች በድንገት ሥራ አጥተው ርዳታ ጠባቂ መሆናቸውን ነግረውናል። ስሙን መግለፅ ያልፈለገ አንድ የ42 ዓመት አባት፤ " ወደ ትውልድ ቦታችሁ ሂዱ ተብለን ባሌ መጣሁ። እናትና አባቴ ሞተዋል ምንም ዘመድ የለኝም ልጆቼን ይዤ ሜዳ ላይ ወጣሁ" - ብሎናል።

ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያድምጡት።