የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ይፈጸምባቸዋል በተባሉ ሆቴሎች እና ድርጅቶች ላይ ርምጃ ተወሰደ

ፎቶ ፋይል፦ አዲስ አበባ ከተማ

በኢትዮጵያ የጸጥታ ኀይሎች፣ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ይፈጸምባቸዋል በተባሉ ሆቴሎች፣ ቡና ቤቶች እና ምግብ ቤቶች ላይ፣ ርምጃ እየወሰዱ እንደኾነ፣ የከተማዪቱ አስተዳደር ትላንት ኀሙስ አስታወቀ።

የዐዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ፣ በሕዝቡ በቀረበለት ጥቆማ፣ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት በሚፈጸምባቸው ድርጅቶች ላይ፣ ርምጃ እየወሰደ እንደኾነ ገልጾ፣ የከተማዪቱን አንዳንድ የእንግዳ ማረፊያ ኪራይ ቤቶችንም እንደፈተሸ ጠቅሷል።

ይህን፣ “በሰው እና በእግዚአብሔር የተጠላ አጸያፊ ድርጊት” ለሚፈጽሙ እና ፈጽመውም በሚገኙ ሰዎች ላይ፣ ቢሮው ርምጃ መውሰዱን እንደሚቀጥል፣ የርእሰ መዲናዪቱ አስተዳደር፣ በፌስቡክ ገጹ ላይ ባሰፈረው ጽሑፍ አመልክቷል።

የመብት ተሟጋች ቡድኖች፥ በኢትዮጵያ፣ የተመሳሳይ ጾታዊ ግንኙነቶችን የሚፈጽሙ ግለሰቦች፣ ማንነታቸው ሲታወቅ፣ ከፍተኛ ጥቃት እና መገለል እንዳይደርስባቸው ስለሚፈሩ፣ ራሳቸውን ደብቀው ተገደዋል፤ ይላሉ።

በኢትዮጵያ፣ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት በሕግ የተከለከለ ነው። ይኹን እንጂ፣ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት በመፈጸማቸው የተፈረደባቸው ሰዎች ስለመኖራቸው የሚያሳዩ ዘገባዎች አልተሰሙም።

በሌላ ተያያዥ ዜና፣ ኢትዮጵያ ውስጥ፣ የተመሳሳይ ጾታዊ ግንኙነት ፈጻሚዎች፣ በማኅበራዊ ብዙኀን መገናኛዎች ላይ፣ ከፍተኛ ወከባ እንደሚደርስባቸው ተገልጿል፡፡

በተለይ ቲክቶክ የተሰኘው የማኅበራዊ ትስስር መድረክ፣ በተመሳሳይ ጾታዊ ግንኙነት ፈጻሚዎች ላይ፣ ግርፋትንና በስለት መወጋትን የመሳሰሉ አካላዊ ጥቃቶች እና ግድያዎች እንዲፈጸሙባቸው የሚጠይቁ ጥሪዎች ይቀርቡባታል፤ በሚል ቢከሠሥም፣ እነኚኽን ጥሪዎች አለማንሣቱን በመጥቀስ ይወነጅላሉ።

ድርጊቱ በወንጀል የሚያስጠይቅ እንደኾነ የገለጹ የተለያዩ የአፍሪቃ ሀገራት፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ፣ በፈጻሚዎቹ ግለሰቦች ላይ ጥብቅ ርምጃ ሲወስዱ ቆይተዋል፡፡ በቅርቡም፣ ተመሳሳይ ሕግ ያጸደቁት ጋና እና ዩጋንዳን ጨምሮ በርካታ የአህጉሩ መንግሥታት፣ ጥብቅ ሕጎችንና የቅጣት ውሳኔዎችን ተግባር ላይ በማዋል ላይ ናቸው።